የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ለ25 ህፃናት የልብ ቀዶ ጥገና የሚውል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሁለትዮሽ ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጠናክር መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋዎች ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ካፒታል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ የሎጂስቲክስ ልምድና ሰብአዊ ትብብር ጋር በማጣመር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል።
በዚህም ሁለቱ ሀገራት በመሠረቱት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጤናው ዘርፍ ጠንካራ ትብብር እያደረጉ ሲሆን፣ ሀገሪቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላትን አጋርነት ለማሳየት የልብ ቀዶ ጥገና ለሚያስፈልጋቸው ህፃናት ህክምና የሚውል ቁሳቁስ ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ የህክምና ማዕከል ለግሳለች።
በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ አማካኝነት የተበረከተው ይህ ድጋፍ 25 ህፃናት የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
በርክክቡ ወቅት የኢሚሬትስ ቀይ ጨረቃ ባለስልጣን የድጋፍ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳርሃን አል ነያዲ፣ ድጋፍ የተደረጉ ቁሳቁስ በልብ ህሙማን ህፃናት ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሚያመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ድጋፉ ህፃናቱ ህይወት አድን የልብ ህክምና እንዲያገኙ ከማገዙም በላይ በኢትዮጵያና በኤምሬቶች መካከል ያለውን ጠንካራ የሰብአዊ ትብብር የሚያሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ህሩይ አሊ በበኩላቸው፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥት ላቀረበው የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ግብአት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ድጋፉ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ትብብር በህፃናትና በቤተሰቦች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ህያው ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል በዓመት ከ700 በላይ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና የሚሰጥ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺህ በላይ ህፃናት የልብ ቀዶ ጥገና ህክምናን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
በሐምራዊት ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: