Search

የአሰብ ትዝታ እና የቀይ ባሕር የህልውና ጥያቄ በታሪክ መነጽር

ማክሰኞ ኅዳር 08, 2019 107

የቀይ ባሕር ውብ የንግድ ማዕከል በነበረችው አሰብ ላይ የተዘረጋው የክፋት ሤራ የትውልድ ቁጭት እና የማይሽር የሥነ-ልቦና ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ነው።

በ1983 ዓ.ም በተከሰተው አሳዛኝ ታሪካዊ ሂደት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እትብታቸው ከተቀበረበት ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

ከመረጃዎች እንደምንረዳው ከ120 ሺህ እስከ 150 ሺህ የሚሆኑ ሲቪሎች፣ ሠራተኞች እና የሠራዊት ቤተሰቦች ያለምንም ካሳ ንብረታቸው ተዘርፎ ከአሰብ እንዲወጡ ተደርገዋል።

እነዚህ ዜጎች ባላሰቡበት ቅጽበት እንዲወጡ የተደረገው ዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ መልኩ ዕድሜ ልካቸውን ለፍተው ያፈሩትን ሀብት ተነጥቀው ነው፡፡

ኢትዮጵያውያኑ የጥርስ ወርቃቸው ጭምር በሰደፍ እስከመነቀል የደረሰ ኢሰብአዊ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል።

ዛሬም ድረስ ከአሰብ ቅርብ ርቀት በምትገኘው ኮምቦልቻ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙት የአሰብ ተፈናቃዮች ወገኖቻችን የቤታቸውን ካርታዎች፣ ሕጋዊ የወራሽነት ሰነዶች እና የከተማዋን ውብ ትዝታዎች እንደ ሕያው የታሪክ ምስክር ይዘው ይኖራሉ።

አሰብን እንደ ፍቅር ከተማ የሚያስታውሷት እነዚህ ዜጎች የደረሰባቸው መከራ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን የማንነት መቋረጥ ጭምር እንደሆነ በቁጭት ያወሳሉ።

የዚህ ሰቆቃ ሌላኛው ተጎጂ በባሕር ዳርቻ እና በደቡባዊ ቀይ ባሕር ክልል የሚኖረው የቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ነው።

ከወገኑ ተቆርጦ በሌላ አስተዳደር ሥር እንዲወድቅ የተደረገው ይህ ሕዝብ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የግዳጅ መፈናቀሎች ተፈጽመውበታል።

ግፉ ሲበዛም ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቀይ ባሕር አፋሮች ግፍን ሸሽተው መሰደዳቸው የክፋቱን መጠን እና የድርጊቱን አሳዛኝ ገጽታ በግልጽ ያሳያል።

ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ሀብት እና ጥረት ተገንብቶ የነበረው የአሰብ ነዳጅ ማጣሪያ ዛሬም ድረስ ያለጥቅም ወድቆ መገኘቱ ታሪክ የመዘገበው ሌላ የክፋት ሤራ ነው።

ይህ እጅግ ዘመናዊ መሠረተ ልማት በወቅቱ የነበሩ የተሳሳቱ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እና ሤራዎች ያለአንዳች አገልግሎት መቆሙ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ለመነጠል የተሄደበትን የታሪካዊ ጠላቶቻችን የዘመናት የክፋት ሤራ ማሳያ ነው።

አሰብ መነጠቁ እና ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በር እንድትርቅ በመደረጉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ኪሣራ አድርሶባታል። የደኅንነት ስጋትም ደቅኖባታል፡፡

በወቅቱ የነበሩት መሪዎች "አሰብ የግመል መጠጫ ይሆናል" በሚል ፖለቲካዊ ብስለት የጎደለው አልያም የክፋት ውሳኔ ወስነዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ አሰብ ዛሬ የግመል መጠጫ እንኳን ለመሆን ያልበቃ ባድማ ምድር ሆኗል፡፡

እነዚህ ጉዳዮች ናቸው የቀይ ባሕር ጉዳይ የፍጆታ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጥያቄ ያደረጉት።

ይህንን ታሪካዊ እና ጂኦፖለቲካዊ እውነታ መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር ለመመለስ የምታነሳው ጥያቄ ችሮታን መጠየቅ ሳይሆን፣ ወደ ራሷ ታሪክ፣ ላብ እና ተፈጥሯዊ የህልውና መሥመር የመመለስ ሕጋዊ ጥያቄ ነው።

ባለፉት ዓመታት በሤራ ዋጋ እንዲከፍል እና ከባሕር እንዲገለል የተደረገው ሕዝብ ዛሬ በሰላማዊ ድርድር፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሕጋዊ መንገድ መብቱን መጠየቁ የቀጣናውን ሰላም ዘላቂ የሚያደርግ ብቸኛ መንገድ ነው።

አሰብ የነገውን የጋራ ዕጣ ፈንታ በፍትሕ ለመገንባት፣ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: