በኢትዮጵያ በተሠሩ ሰፊ ሥራዎች የብሔር ብሔረሰቦች መስተጋብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ መምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትግሉ መለሰ ገልጸዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል በመተባበር 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማስመልከት ለሦስቱ ተቋማት አመራሮች እና ሠራተኞች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥተዋል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ትግሉ መለሰ፣ “በብዝኃነት የደመቀች፤ በምክክር የፀናች ሥልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዘንድሮው በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በጀማ ከተማ ሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንደሚከበር አስረድተዋል።
በዓሉን አስመልክቶም ከ33 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች ስለ ሕገ መንግሥት፣ ፌዴራሊዝም እና የመንግሥት አስተዳደር ግንዛቤ ለማስጨበጥ መታቀዱን ጠቁመዋል። ብዝሃነትን የመከባበር፣ የእኩልነት፣ የሰላም እና የአንድነት መሠረት አድርጎ መገንባት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከ4 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈው ሀገራዊ ምክክር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን የጠቀሱት አቶ ትግሉ፣ የምክክሩን ውጤቶች ወደ ተግባር በመቀየር በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
ሥልጡን ማኅበረሰብ ማለትም እርስ በርስ የሚከባበር፣ የሚደማመጥ፣ ችግሮችን በውይይት የሚፈታና የሕግ የበላይነትን የሚያከብር ማኅበረሰብ መገንባትን እንደሚያካትት አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ “የብዝሃነት አስተዳደር በፌዴራል ሥርዓት” በሚል ርዕስ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ ውዲሻ፣ እንዲሁም “የመንግሥታት ግንኙነት ለጠንካራ ፌዴራል ሥርዓት ግንባታ” በሚል ርዕስ በአስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታየ (ዶ/ር) መወያያ ሰነዶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የሕዝቦች አብሮነት እና መከባበር ለሀገራችን ሰላም፣ ልማት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንም ይህንኑ አንድነት እና ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት ወሳኝ መድረክ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: