Search

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች፡- ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ

ማክሰኞ ኅዳር 08, 2019 116

ኢትዮጵያ ተቋማዊ አቅሟንና አጋርነቷን በማጎልበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የሰላም ማስከበር ሚና ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ተቋማዊ አቅሟን በማዘመን፣ የሠራዊቷን ዝግጁነት ማሳደግና ቀጣናዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ አጋርነቷን በማስፋት በዓለም የሰላም ማስከበር ሚናዋን እንደምትወጣም ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ማሠልጠኛ ተቋምና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በጋራ ባዘጋጁት መድረክ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ሥርዓት ለውጥና በባለብዙ ወገን ትብብር መዳከም ተግዳሮቶች ውስጥ የሰላም ማስከበር ሚናዋን የምታስቀጥልባቸው ስትራቴጂዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተሳትፎ የዓለም አቀፍ ግዴታ ብቻ ሳይሆን የሚያኮራ ብሔራዊ ታሪክና ወሳኝ ስትራቴጂያዊ ሀብት ነው።

ኢትዮጵያ በ1950ዎቹ በኮሪያ ጦርነት ከተሳተፈችበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ከ70 በላይ ዓመታት ውስጥ ከ180 ሺህ በላይ የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማሰማራት ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነት ያላትን ጽኑ አቋም በተግባር ማሳየቷን አንስተዋል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተቋማዊ አቅምን ማዘመንና ፖሊሲዎችን፣ የህግ ማዕቀፎችንና የአሠራር ሥርዓቶችን ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር ለማጣጣምም ይሠራል ብለዋል።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ከምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጋር ያለው ትብብር እንደሚጠናከርና ዘላቂ የሀብት ምንጮችን ለማስፋት ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን የወደፊት የሰላም ማስከበር ስትራቴጂ ከዓለም አቀፍ ግዴታ፣ ከአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ከሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ደኅንነት ጥቅሞች ጋር በማቀናጀት እንደሚመራም ተናግረዋል።

ከመድረኩ የተገኙ ምክረ-ሃሳቦች በአግባቡ ተሰንደው የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት በመሥራት ወደ ተጨባጭ ፖሊሲና ተግባራዊ መርሐ ግብር እንዲቀይሩት ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: