ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ ዙሪያ የሚወጡ ህጎችን በመተግበር ረገድ የሚደነቅ ሥራ እየሠራች መሆኗን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ የኢትዮጵያ ተወካይ አይሳቱ እንጃይ ገለጹ።
4ኛው የአፍሪካ የመፈናቀል ጉዳይ የግሉ ዘርፍ ፎረም (AFD2026) መድረክ በአዲስ አበባ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ የኢትዮጵያ ተወካይ አይሳቱ እንጃይ ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ ዙሪያ የሚወጡ ህጎችን በመተግበርና በሰብዓዊ አያያዝ ላይ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ እንደምትሆን ገልጸዋል።
የስደተኞችንና የተፈናቃዮችን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ማረጋገጥ የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
በአፍሪካ የመፈናቀል ችግርን ከሰብዓዊ እርዳታ ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ መፍትሔ ለመቀየር ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የስደተኞችና የተፈናቃዮች ጉዳይ በሰብዓዊ ዕርዳታ ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የኢኮኖሚ ተሳትፎን፣ የሥራ ዕድልን እና ዘላቂ ልማትን በሚያረጋግጡ አማራጮች መደገፍ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ የስደተኞችን ጉዳይ በሀገራዊና በአካባቢያዊ የልማት ዕቅዶች ውስጥ ለማካተት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
የገበያ አቅምን ለማስፋት፣ የኢንዱስትሪ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣ የመቋቋም አቅምን ለማሳደግና ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ እየሠራች ነው ብለዋል።
ስደተኞችን የተመለከቱ የተሻሻሉ ፖሊሲዎች ወደ ተጨባጭ ውጤት መቀየር ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህም የተሻሉ የሥራ ዕድሎችን፣ አስተማማኝ አገልግሎቶችን፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን፣ የኑሮ መሠረት ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ዛሬ በተጀመረውና በአፍሪካ የስደተኞችና የተፈናቃዮች ጉዳይ ላይ ያተኮረው (AFD 2026) መድረክ የግሉን ዘርፍ፣ መንግሥታትን፣ ባለሀብቶችንና የልማት አጋሮችን በማሳተፍ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያለመ ነው።
ግጭት፣ የጸጥታ ችግር፣ የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት በአፍሪካ የሰዎች መፈናቀልን እያባባሱ ከሚገኙ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል መሆናቸውም በመድረኩ ተጠቅሷል።
በመሆኑም ስደተኞችና ተፈናቃዮች የዕርዳታ ተቀባዮች ብቻ ሳይሆኑ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳታፊና ለልማት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዜጎች እንዲሆኑ ማስቻል የመድረኩ ትኩረት ነው።
ለ3 ቀናት በሚቆየው በዚሁ መድረክ “ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን ከዕርዳታ ጥገኝነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ራስን መቻል ማሸጋገር” በሚል መሪ ሐሳብ ውይይት እየተደረገ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ልምዷን የምታጋራበትና የምትቀስምበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በመሐሪ ዓለሙ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: