በዓለም አቀፍ የጤና አቅርቦት ሥርዓት ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በጋራ በመፍታት፣ የመድኃኒት እጥረትን ለመቀነስ እና ጥራት ያላቸው የሕክምና ግብዓቶች በተፈለገው ጊዜ አና ቦታ እንዲደርሱ ለማስቻል የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
19ኛው ዓለም አቀፍ የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። ጉባኤው በዋናነት የመድኃኒት እጥረትን መቅረፍ በሚቻልባቸው የጋራ መፍትሔዎች ላይ እንደሚያተኩር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመክፈቻ ንግግራቸው አስታውቀዋል።
የመደመር መንግሥት የጤና አቅርቦት ሰንሰለቱን ለማሻሻል እና ለማዘመን በትኩረት እየሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት ዓመታት የጤና ፖሊሲዎችን በማሻሻል አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን፣ የመድኃኒት አቅርቦቱን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ እና ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ሰፊ ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል።
በዚህም የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን በማሳደግ የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት፣ የሀገር ውስጥ አምራቾች ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የመድኃኒት አቅርቦት ያላቸውን ድርሻ 44 በመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
ይህንን አቅም ይበልጥ ለማሳደግ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የጠቆሙት ዶ/ር መቅደስ፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እና በዘርፉ ለሚሰማሩ አልሚዎች እና መድኃኒት አምራቾች አስፈላጊው ምቹ መደላድል መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
"ለቀጣዩ ዘመን የጤና አቅርቦት ሰንሰለቶች ፖሊሲን፣ ገበያን፣ ካፒታልን እና ተደራሽነትን እንደገና መመርመር" በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ጉባኤ፤ የጤና አቅርቦት ሥርዓቱን ከዘመኑ ጋር በማስማማት ዘላቂ፣ ተደራሽና ችግሮችን መቋቋም የሚችል ለማድረግ ያለመ ነው።
ጉባኤው የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የአቅርቦት ሰንሰለት አቅምን ማጠናከር፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ፣ የገንዘብ እና የኢንቨስትመንት አቅምን ማስፋፋት እንዲሁም የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን ማበረታታት በሚሉ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ይመክራል።
መድረኩ የተለያዩ ሀገራት የጤና ባለሙያዎችን፣ የመንግሥት ተቋማትን፣ የመድኃኒት አምራቾችን፣ ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶችን፣ ተመራማሪዎችን እና የግሉን ዘርፍ ተወካዮች በአንድ ላይ አሰባስቧል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር፣ የግዥ እና ስርጭት ሥርዓቱን ለማዘመን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማበረታታት እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች ለማካፈልና ከሌሎች ሀገራት ልምድ ለመቅሰም ያስችላል።
ከኅዳር 8 እስከ 10 ቀን 2019 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው ይህ ጉባኤ፤ ከውይይት ባለፈ ወደ ተግባር የሚቀየሩ የትብብር፣ የኢንቨስትመንትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነቶችን በማስፈጸም ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካውያን የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል።
በዘሐራ መሐመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: