ጦርነት ከውድመት፣ ከሞት እና ከአካል ጉዳት ውጪ ምንም ጥቅም እንደሌለው መገንዘባቸውን የተሃድሶ ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ተናግረዋል።
"ጦርነት ይበቃናል፤ ሰላም ይሻለናል" በሚል ትጥቃቸውን በማውረድ መቐለ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሃድሶ ማዕከል ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ ከ7 ሺህ 200 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ሥልጠናቸውን አጠናቅቀዋል።
ሠልጣኞቹ በተሳሳተ መንገድ አሁንም በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ወገኖቻቸው ካሉ የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለ26 ቀናት በተሰጠው የተሃድሶ ሥልጠና ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ሕይወታቸውን በአግባቡ መምራት እና ወደ ሥራ መሰማራት የሚያስችላቸውን ክህሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ከሠልጣኞቹ መካከል አንዱ በሰጠው አስተያየት፤ "በዚህ የተሃድሶ ሥልጠና ሰላም ከምንም በላይ ጠቃሚ መሆኑን ተምሬያለሁ፤ ጦርነት ከውድመት፣ ከሞት እና ከአካል ጉዳት ውጪ ምንም ጥቅም እንደሌለው ተገንዝበናል" ብሏል።
ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ በበኩሉ ወደ ሰላም መስመር ያልመጡ ካሉ ከማይጠቅመው መንገድ ወጥተው እነሱ የመረጡትን የሰላም መንገድ እንዲመርጡ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ እንደገለጹት፤ ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ ክልል በስድስት ማዕከላት ማለትም ሽሬ፣ አክሱም፣ አድዋ፣ አዲግራት፣ ማይጨው እና መቐለ ወደ 47 ሺህ የሚጠጉ የቀድሞ ታጣቂዎች ተመዝግበዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያ ዙር ዕድል ያገኙት ከ7 ሺህ 200 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ሥልጠናቸውን ማጠናቀቃቸውን ጠቁመው፤ መርሐ ግብሩ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር አወሉ አብዲ በበኩላቸው፤ የተሃድሶ ሠልጣኞቹ በሀገር ውስጥ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲሁም አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ሲያሟሉ በውጭ ሀገር ጨምር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ ሥልጠናውን ከወሰዱት መካከል ከሻለቃ አዛዥ እስከ ኮር አመራር ድረስ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
እነዚህ አካላት ራሳቸውን ከጥፋት በማራቅ ወደ ሰላም እና ልማት መምጣታቸው ለትግራይ ብሎም ለመላው ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እስካሁን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ከ93 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሲቪል ሕይወት መመለስ ችሏል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: