Search

ካሉብ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጫና ማጣሪያ ፕሮጀክት ሥራ መጀመሩ ለኢንዱስትሪዎች መነቃቃት ትልቅ ምዕራፍ ነው

ማክሰኞ ኅዳር 08, 2019 122

የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም ከቃል ወደ ተግባር የቀየረው ካሉብ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጫና ማጣሪያ ፕሮጀክት ሥራ መጀመሩ ለሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ፣ ለኢንዱስትሪዎች መነቃቃት እና ለቀጣናዊ ትሥሥር ትልቅ ምዕራፍ ነው።

በካሉብ የጋዝ ማውጫና ማጣሪያ ኩባንያ የውጭ ክፍል የሥራ ሂደት ኦፕሬተር አስፋው ወርቁ የፕሮጀክቱን መጀመር አስመልክቶ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የነዳጅ ዋጋ መናር ትልቅ ጫና እንደነበረውና አሁን ላይ ጋዝ ማምረት መጀመሩ በትራንስፖርት ዘርፍ ትልቅ መፍትሔ እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

ከውጭ በዶላር የሚገባውን የነዳጅ ግዥ በጀት በመቀነስ ረገድም አሁን ላይ የሚደረገው የጋዝ ማጣሪያና ማከፋፈል ሥራ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

ነዳጅን ከምድር ውስጥ አውጥቶ በማጣራት እና በማጠራቀሚያ ኮንቴነሮች በመሙላት ለተጠቃሚው ማድረስ መጀመሩ የሀገራችንን የኢነርጂ ዋስትና አስተማማኝ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

በማዕድን ሚኒስቴር የካሉብ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ቢሮ የፕሮጀክት ማኔጀር አቶ ታደሰ ሉሌ በበኩላቸው፣ ኩባንያው ከገባው የውል ስምምነት ማጠናቀቂያ በኋላ ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ለኢትዮጵያ በባለቤትነት እንደሚያስረከብ ገልጸዋል።

በዚህም የአካባቢው ወጣት ኢንጂነሮች በሂደት ቴክኖሎጂውን በመልመድ የሀገራቸውን የተፈጥሮ ሀብት በራሳቸው አቅም ማምረት እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ፕሮጀክቱ የተፈጥሮ ሀብት ማውጣት ሂደት ብቻ ሳይሆን፣ ወጣቶች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚማሩበትና አቅማቸውን የሚገነቡበት ትልቅ የትምህርት ማዕከል ሆኗል።

በአካባቢው ከሚገኙ ወጣቶች መካከል አብዱልከሪም አብዱላሂ እንደገለጸው፣ ኩባንያው በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን እውቀት በተግባር እንዲለማመዱና ለሀገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ሰፊ ዕድል ፈጥሮለታል።

ጸጥ ባለው የካሉብ ሞቃታማ ምድር ስር ከሚፈልቀው የተፈጥሮ ጋዝ ባሻገር፣ ትልቁ ሀብት ሀገሩን በእውቀት እና በክህሎት ማልማት የሚችል ትውልድ መፍጠር እየቻለ መሆኑ በፕሮጀክቱ በግልጽ እየታየ ይገኛል።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: