Search

የአየር ንብረት ፋይናንስ ለታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ፍላጎቶች ምላሽ በሚሰጥና ተደራሽ በሆነ መልኩ ሊቀርብ ይገባል - ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ኅዳር 08, 2019 105

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የCOP32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የአየር ንብረት ፋይናንስ በሚያስፈልገው ደረጃ፣ በተደራሽ መንገዶች እና ለታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ፍላጎቶች ምላሽ በሚሰጥ መልኩ እንዲቀርብ ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በCOP31 ላይ "ከውጥን ወደ ተግባር፡ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም (GEF)፣ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ፈንድ (LDCF) እና በልዩ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ (SCCF) አማካኝነት የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ" በተሰኘው የከፍተኛ ኃላፊዎች ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

በንግግራቸውም ለታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ሀገራዊ ውጥኖችን ወደ ተግባር ለመቀየር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሀብቶች በቂ በማይሆኑበት ጊዜ ትግበራ እንደሚዘገይ፣ ተጋላጭነት እንደሚባባስ እና በጋራ ጥረት ላይ የሚኖረው እምነት እንደሚዳከምም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ COP32ን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ዝግጅት ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም (GEF) ቤተሰብ ድጋፍን ጨምሮ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ፈንድ (LDCF) እና በልዩ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድን (SCCF) ለማጠናከር የተጀመረውን የሀብት ማሰባሰብ ጥረት ሚኒስትሩ በደስታ ተቀብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሁሉም አጋሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ዝግጁነትም አረጋግጠዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: