41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ዓመታዊ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
ኢቲቪ 57 የዜና መሰናዶ ጉባዔውን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል።
ዋና ዳይሬክተሩ በቆይታቸው፥ በ41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ጉባዔ በርካታ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ገልፀው፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ የአፍሪካ የጋራ የትምህርት ምዘና ማዕቀፍ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
የዚህ ማዕቀፍ ዓላማ በአፍሪካ ሀገራት ያለውን የተለያየ የተማሪዎች ምዘና ሥርዓት ወጥ በማድረግ ዜጎች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሲዘዋወሩ ወጥ በሆነ አሠራር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ማዕቀፉ የትምህርት ምዘና እና ፈተናን ከሌሎች ሀገራት ወስዶ ከራስ ባህል፣ የአሰራር ሂደት እና ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የትምህርት ምዘና እና ፈተና ሥራን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማሻገር ያለመ መሆኑንም ዶ/ እሸቱ ጠቁመዋል።
ሀገራት ትብብራቸውን እንዲያሳድጉ እና በግላቸው ሲያደርጉት የነበረውን ዘርፉን የማሻሻል ጥረት በጋራ በማከናወን ውጤት እንዲያመጡ የሚያስችል ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የጋራ ማዕቀፉ የአፍሪካ አጀንዳ 2063ን በመደገፍ የአፍሪካ ኀብረት በትምህርቱ ዘርፍ ለማምጣት ያሰበውን ለውጥ ሊያፋጥን የሚችል ስለመሆኑም ነው የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ያነሱት።
በሰለሞን ከበደ
#ኢቢሲዶትስትሪም #አፍሪካ #ትምህርት #ምዘና