በኦሮሚያ ክልል፣ በቦረና ዞን በፀጥታ ችግር ምክንያት ፈራርሰው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለመጪው የትምህርት ዘመን ዝግጁ እየተደረጉ መሆናቸው ተገልጿል።
ትምህርት ቤቶቹ ያስተናገዱት ጉዳት የመማር፣ ማስተማር ሂደቱን ያስተጓጎለ እንደነበር ተማሪዎች እና መምህራን ለኢቲቪ ተናግረዋል።
አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ከመገንባታቸው በተጨማሪ የተጎዱት እድሳት ተከናውኖላቸው ለመጪው የትምህርት ዘመን ዝግጁ እየተደረጉ መሆኑንም ነው የገለፁት።
ትምህርት ቤቶቹ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ የገለፁት የዞኑ ጽ/ቤት ኃላፊ ዮናስ በሪሶ፤ በዚህ ረገድ ማህበረሰቡ የድርሻውን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ጥገናው በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በአካባቢው ማህበረሰብ ጥምረት የተካሄደ እንደሆነም ኃላፊው አክለዋል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ለመጪው የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት ከ7.4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት መደረጉ ተጠቅሷል።
በአፎሚያ ክበበው
#ኦሮሚያ #ቦረና #አማራ #ትምህርት