ሰብአዊ ክብርንና የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት ማዕከል በማድረግ የመዲናዋን ገጽታ የለወጠ እና ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ ቱሪዝም ዝግጁ የሚያደርግ አዲሱ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ቀደም ሲል የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ተሞክሮ በመቀመር በ57 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፤ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ ተመርቋል።
ሰውን ማዕከል ያደረገው ይህ ፕሮጀክት ሰፋፊ መንገዶችን ከመገንባት ባለፈ የከተማን ውበት፣ ምቾት እና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር በአንድ ላይ ያቀናጀ ዘመናዊ መሠረተ ልማትን እውን አድርጓል።
በውስጡም ደረጃቸውን የጠበቁ የአስፋልት መንገዶች፣ ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መንገዶች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች እና የተቀናጁ የመሬት ውስጥ መሠረተ ልማቶች ተካትተውበታል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለንጹሕ ኢነርጂ ልማት የሰጠችውን ትኩረት በሚያጠናክር መልኩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች እና ከ5 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች ተገንብተውለታል።
የመደመር መንግሥት ከተሞችን የሥራ ፈጠራ፣ የንግድ፣ የዕውቀትና የባህል ማዕከላት በማድረግ ለሕዝብ ቁጥር ዕድገትና ለአየር ንብረት ለውጥ ዘላቂ ምላሽ የመስጠት ዕሳቤን በተግባር ያሳየው ይህ ልማት፣ ለነዋሪዎች ማኅበራዊ ሕይወትና ጤና ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።
በዚህም መሠረት የታደሱ ትምህርት ቤቶች፣ ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት፣ የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች እና ሕዝባዊ ፕላዛዎች ተገንብተው ነዋሪዎች ንጹሕና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመዝናኛ ስፍራ እንዲያገኙ ተደርጓል።
በኮሪደሮቹ ዙሪያ የተሠሩት አዳዲስ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የንግድ ማዕከላት እና የኪነ-ጥበብ ስፍራዎችም የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ሌሊትና ቀን ሕያው በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ፕሮጀክቱ በግንባታው ወቅት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ መሃንዲሶችና ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር የትራፊክ ፍሰትን በማቀላጠፍ የከተማ ቱሪዝምን በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ ነው።
ወደ ታሪካዊ ስፍራዎች የሚያቀኑ ቱሪስቶች በቅድሚያ በከተማዋ እምብርት በሚገኙ ውብ ፓርኮችና በምሽት መብራቶች በደመቁ ኮሪደሮች ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ በማስቻል ልማቱ የኢትዮጵያን ብልጽግናና ዘመናዊነት ለዓለም የሚያሳይ መስኮት ሆኗል።
በመሆኑም የመሠረተ ልማት ግንባታን ከሕዝብ የዕለት ተዕለት ሕይወት መሻሻል ጋር ያስተሳሰረውና የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረው ይህ ታሪካዊ የኮሪደር ልማት ሥራ፣ ለዛሬው ትውልድ ምቹ ከተማን ከመፍጠር ባለፈ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ ሀገራዊ ቅርስና የልማት ዐሻራ ሆኖ የሚቀጥል ነው።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: