አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ ውበትና ግርማ ሞገስ የሚያላብሷትን አዳዲስ የልማት ሥራዎች እያስመረቀች የከተማዋን ገጽታ በፍጥነት እየቀየረች ትገኛለች። ይህ የለውጥ ጉዞ በትናንትናው ዕለት በይፋ በተመረቀው 3ኛው ዙር የኮሪደር ልማት አማካኝነት ዳግም በተጨባጭ ታይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ኢትዮጵያ መሠራት፣ መገንባትና ማማር እንደምትችል በቂ ማሳያዎች ታይተዋል” ሲሉ የሀገራችንን የማድረግ አቅምና የተግባር ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ሆኖም እስካሁን የተመዘገቡት አስደናቂ ውጤቶች የመጨረሻ ግቦች ሳይሆኑ፣ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ የመጀመሪያ ምልክቶች መሆናቸውንም በግልጽ አስቀምጠዋል።
ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑት የ1ኛው እና የ2ኛው ዙር የኮሪደር ልማቶች የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት፣ ውበትና የነዋሪዎችን የአኗኗር ዘይቤ በጉልህ ቀይረዋል። በትናንትናው ዕለት የተመረቀው 3ኛው ዙር ልማት ደግሞ ይህንን ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ነው።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ገና ያልተነካች ሀገር ናት፤ ይህ እስካሁን የተሠራው ሥራ ጅምር ብቻ ነው፤ ገና ብዙ የሚቀር ሥራ አለን” በማለት ያልተነካ ሀብትና ዕምቅ አቅም አመላክተዋል።
ይህም የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ገና በማለዳው ላይ መሆኑንና ወደፊት ከዚህ እጅግ የላቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በመላው ሀገራችን እንደሚከናወኑ የሚያበስር ነው።
ይህ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን በጋራ ከቆሙና በአዲስ የሥራ ባህል ከተንቀሳቀሱ የማይቻል ነገር እንደሌለ በተግባር ያሳየ ነው። ከ“አይቻልም” እና “አይሠራም” አስተሳሰብ በመውጣት፣ በራስ አቅምና ዕውቀት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ልምምድ ዛሬ ላይ ሀገራዊ ባህል እየሆነ መጥቷል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: