በ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቀልብ ከመሳብ ባለፈ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ከመሰረቱ እየቀየረ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የመደመር ንግሥት የቱሪዝም ልማት አቅጣጫ የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን በማልማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ ባለፈ፣ ልማቱን ከአካባቢው ማኅበረሰብ ሕይወት ጋር በቀጥታ ማስተሳሰር ላይ ያተኮረ ነው።
ለዓመታት በተፈጥሮ ውበትን ታድሎ ነገር ግን በመሰረተ ልማት እጦት ምክንያት ጸጋው ተሸፍኖ የቆየው የወንጪ አካባቢ ዛሬ በተቀናጀ ልማት ገጽታው ተቀይሮ ደማቅ የቱሪዝም እና የንግድ ማዕከል ሆኗል።
በተለይም መንግሥት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማልማት የአካባቢው ማኀበረሰብ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን በዘረጋው አቅጣጫ መሰረት የወንጪ ነዋሪዎች የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ሕይወታቸው በባህላዊ ግብርና እና በከባድ የጉልበት ሥራ ብቻ ተወስኖ ለዓመታት በድካም ያሳለፉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ወልደ ጊዮርጊስ የፕሮጀክቱ መገንባት የኑሮ ዘይቤያቸውን ሙሉ በሙሉ እንደቀየረው ይናገራሉ። በመሆኑም ምቹ እና ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ጨምሮ እንደተሰራላቸው ይመሰክራሉ፡፡
"ድሮ ድንች እየቆፈርን እና ፈረስ ጭነን ወደ አምቦ ስንመላለስ አድረን ነበር የምንገባው፤ ዛሬ ግን ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ተሠርቶልን፣ በራፋችን ድረስ መንገድ ተዘርግቶልን አዋራ እና ጭቃ ሳይነካን የፈለግንበት ቦታ ደርሰን በደስታ እንመለሳለን" በማለት ነው ያገኙትን ጥቅም የሚገልጹት።
"ይህንን ትንሣኤ ለፈጠሩልን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትልቅ ምስጋና አለን" ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
በአከባቢያቸው የሚገኘው ጥንታዊው ወንጪ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን በእድሳት ላይ በመሆኑም መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሸለመ አብዲሳ በበኩላቸው ከአስቸጋሪ የኑሮ ዘይቤ ተላቅቀው በኤሌክትሪክ ኃይል እና በምቹ መኖሪያ ቤት ዘመናዊ ኑሮ እየመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ወንጪ በጎብኚዎች እና በተሽከርካሪዎች በመድመቋ ለብዙዎች የሥራ እና የገቢ ምንጭ ማስገኘቱን አንስተዋል።
"ትናንት በእንጨት አብስለን ነበር የምንበላው ዛሬ በኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነናል፤ በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ወንጪ በሕዝብ እና በተሽከርካሪዎች ተጨናንቃ አዲስ አበባ ፒያሳን ትመስላለች" በማለት በአካባቢው የተፈጠረውን የኢኮኖሚ መነቃቃት አስረድተዋል።
በፕሮጀክቱ የስራ እድል የተፈጠረላቸው የአካባቢው ተወላጅ አቶ ፀጋዬ ተረፈ እንዳሉት ደግሞ፤ ወንጪ ዓመቱን ሙሉ ለምለም ከመሆኗ ባሻገር የተፈጥሮ ፍልውኃዎች፣ የማዕድን ውኃዎች፣ የጀልባ ሽርሽር እና የፈረስ ግልቢያ አገልግሎቶች የሚሰጡባት ድንቅ ስፍራ ናት።
ቀደም ሲል በመንገድ፣ በመብራት እና በውኃ እጦት ተገድቦ የነበረው የጎብኚዎች ፍሰት አሁን መሰረተ ልማቶቹ በመሟላታቸው ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የተፈጥሮ ጸጋን ከዘመናዊ ልማት ጋር ያዋሃደው የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ለአካባቢው ነዋሪዎች የብልጽግና በር ከመክፈቱም በላይ ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በአግባቡ ከተጠቀመች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደምትችል ህያው ምስክር ሆኗል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: