Search

አደይ አበባ ስታዲየም: የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተስፋ እና የ2028 የአፍሪካ ዋንጫ ራዕይ

ሓሙስ ኅዳር 10, 2019 196

ኢትዮጵያ በስፖርቱ መስክ፣ በተለይም በእግር ኳስ የቀድሞ ገናና ስሟን ለመመለስና የአፍሪካ የስፖርት ማዕከል ለመሆን የምታደርገው ጥረት አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

በአዲስ አበባ ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት የሆነው፤ ከቦሌ መድኃኔዓለም በጎላጉል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ፣ ከቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ሞኤንኮ፣ ከቦሌ ትምህርት ቤት እስከ አደይ አበባ ሞዴል መንደር፣ ከኢምፔሪያል ሆቴል እስከ ሻላ ፓርክ፣ ከቺቺኒያ እስከ ቦሌ ሩዋንዳ፣ ከአደይ አበባ ስታዲየም እስከ ቦሌ መንገድ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን የሚያጠቃልለው እና በአጠቃላይ 57 ሄክታር የሚሸፍነው ዘመናዊ የኮሪደር ልማት ከከተማ ውበት ባሻገር ለኢትዮጵያ ስፖርት መሠረተ ልማት ትልቅ አቅም መፍጠሩን አሳይቷል።

በዚህ ልማት ማዕከል ውስጥ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየምና ዙሪያው፣ የኢትዮጵያን ስፖርት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተያዘውን ራዕይ በተግባር እያሳየ ይገኛል።

ከ62 ሺህ በላይ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው የአደይ አበባ ስታዲየም የጣሪያ ብረት መዋቅር ሥራ ተጠናቅቆ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መቃረቡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ የምሥራች ነው።

ከስታዲየሙ ጎን ለጎን የተገነባው አደይ አበባ ፕላዛ፤ በእግር ኳስ ቅርጽ በተሠሩ የመንገድ መብራቶች፣ ለደጋፊዎች በተዘጋጁ ግዙፍ የቴሌቪዥን መስኮቶች፣ ዘመናዊ የልምምድ ሜዳዎች፣ የብስክሌት መሥመሮች እንዲሁም ከ5 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማቆም በሚችል ሰፊ የመኪና ማቆሚያ ተሟልቶ ለአገልግሎት በቅቷል።

ይህ የተቀናጀ ልማት ብሔራዊ ቡድናችን ጨዋታዎቹን በራሱ ሜዳና በደጋፊው ፊት እንዲያደርግ ከማስቻሉም በላይ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ የካፍ እና የፊፋ መስፈርቶችን ለማሟላት ወሳኝ ድርሻ አለው።

ይህ አዲስ የስፖርት መንደር የዘመናዊነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የሚዘከርበት ሥፍራም ሆኗል። በስታዲየሙ አቅራቢያ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ እግር ኳስ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለታላቁ የስፖርት አባት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ሐውልት መቆሙ ለባለታሪኮቻችን የተሰጠውን ክብር ያሳያል።

ከዚህም ባለፈ የብሔራዊ ቡድናችን መለያ የሆነው የዋልያ ምስል በፕላዛው መካከል መገንባቱ ለመጪው ትውልድ ስፖርተኞችና ወጣት ባለተሰጥኦዎች የአሸናፊነት መንፈስን የሚያስቀጥል ሁኔታን ይፈጥራል።

እነዚህ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ኢትዮጵያ እ.አ.አ. የ2028 የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ያቀረበችውን ይፋዊ የውድድር ጥያቄ በእጅጉ የሚያጠናክሩ ናቸው።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ውድድሩ በየሁለት ዓመቱ እንዲቀጥል በመወሰኑ የ2028 አስተናጋጅነት ፉክክርን ባስቀጠለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ከመንግሥት ሙሉ ዋስትና ጋር የማስተናገድ ፍላጎቷን ማቅረቧ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ውድድሩን እ.አ.አ. በ1962፣ በ1968 እና ለመጨረሻ ጊዜ በ1976 ካስተናገደች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ዳግም ለማዘጋጀት ከሞሮኮ እና ከደቡብ አፍሪካ ጥምረት ጋር ብርቱ ፉክክር ቢጠብቃትም፤ የአደይ አበባ ስታዲየም መጠናቀቅ፣ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መኖር እንዲሁም በሌሎች ክልሎች እየተሠሩ ያሉ ስታዲየሞች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ትስስር እና የአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ የማሸነፍ ዕድሏን ከፍ ያደርገዋል።

በጥቅሉ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉት የስፖርት ሜዳዎች፣ የብስክሌት መንገዶችና ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች ለአንድ ውድድር ብቻ ታስበው የተሠሩ ሳይሆኑ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዘላቂ ዕድገት መሠረት የሚጥሉ ናቸው። ወጣቶች በዘመናዊ ሥፍራዎች እንዲያድጉ፣ እግር ኳስና ብስክሌት በከተማችን ባህል እንዲሆኑ እና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን በድጋሚ የምታስተናግድበት ብሩህ ዘመን እንዲመጣ እነዚህ ፕሮጀክቶች ትልቅ ተስፋ ሰንቀዋል።

በዘረንቶስ ሰለሞን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: