Search

ለ4 ዓመታት በሆድ እብጠት ስትሰቃይ የነበረች ታካሚ 10.5 ኪ.ግ የሚመዝን እጢ በቀዶ ሕክምና ተወገደላት

ሓሙስ ኅዳር 10, 2019 86

በሰቆጣ ከተማ በሚገኘው የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል 10.5 ኪሎ ግራም የሚመዝን እጢ በተሳካ የቀዶ ሕክምና ማስወገድ መቻሉ ተገለፀ፡፡

በሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆነችው የ30 ዓመት ታካሚ ላለፉት አራት ዓመታት በሆድ እብጠት ስትሰቃይ የቆየች ሲሆን፣ በሆስፒታሉ የማህፀንና ፅንስ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዋሲሁን በሚመራ የሰባት የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ውጤታማ የቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል።

በዚህም 10.5 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን እጢ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የተቻለ ሲሆን፣ ታካሚዋ በአሁኑ ወቅት ወደ ማገገሚያ ክፍል ተዛውራ በሐኪሞች የቅርብ ክትትል ሥር ትገኛለች።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ቢምረው በቀዶ ሕክምናው ሂደት በመገኘት ክትትል ያደረጉ ሲሆን፣ ሕክምናውን በስኬት ላከናወኑት የሕክምና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል። አክለውም በቀዶ ሕክምና ክፍሉ የሚታዩ የግብዓትና የመሣሪያ እጥረቶችን ለመፍታት ተቋሙ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

የሕክምና ቡድኑ በበኩሉ፣ ማኅበረሰቡ የሆድ እብጠትንና መሰል የጤና እክሎችን ሲያጋጥሙት በባህላዊ ልምዶች ላይ ተመርኩዞ ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ በቅርብ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራና ሕክምና እንዲያገኝ አሳስቧል።

የተመዘገበው ስኬትም የሆስፒታሉን የቡድን ሥራ፣ የባለሙያዎችን የሙያ ብቃትና ለማኅበረሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት የመስጠት ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ መሆኑን የሰቆጣ ከተማ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: