ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ያከናወነቻቸው አመርቂ ሥራዎች እና ያሳየቻቸው ተጨባጭ ውጤቶች የቀጣናው የስበት ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል።
ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን፣ ግዙፍ ኮንፈረንሶችን እና ዲፕሎማቲክ መድረኮችን በስኬት ማስተናገድ የዝግጅት አቅም ማሳያ ብቻ አይደለም፤ የተቋማዊ ብቃት እና የዓለም አቀፍ እምነት ትልቅ መገለጫም ነው።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ያካበተችው ተሞክሮ እና አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ማዕከል የማድረግ ራዕይ ሀገራችን ከቀጣናዊ ተጽዕኖ ባለፈ ወደ ዓለም አቀፍ ተደማጭነት አሸጋግሯታል።
አዲስ አበባ ቀደም ሲል በዓመት አንዴ ከሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባኤ እና ከጥቂት መድረኮች ያለፈ ሰፊ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ ልምድ አልነበራትም።
ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በመደመር እሳቤ በተከናወኑ ሁለገብ ልማቶች ከተማዋ አዲስ መልክ በመላበስ ከ200 በላይ ጉባኤዎችን በተመሳሳይ ወቅት ማስተናገድ የሚችሉ ዘመናዊ ተቋማትን መገንባት ችላለች።
እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ ሳይንስ ሙዚየም እና አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ያሉ ዘመናዊ ማዕከላት መከፈታቸው አዲስ አበባን የአፍሪካ ቀዳሚ የኮንፈረንስ መዳረሻ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ እጅግ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ብትሆንም፣ ውጫዊ የፋይናንስ ድጋፍ ሳትጠብቅ የራሷን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በቁርጠኝነት ማራመዷ ዓለም አቀፍ እውቅና አስገኝቶላታል።
በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና በዘላቂ ልማት የተጀመረው ይህ ተነሳሽነት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የተባበሩት መንግሥታት አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ COP32 እንድታስተናግድ ለተመረጠችበት ስኬት መሠረት ሆኗል።
ይህንን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ማስተናገድ የኢትዮጵያን ገጽታ ከቀድሞው የችግርና የተረጂነት ትርክት በማላቀቅ በልማትና በብልጽግና ጎዳና ላይ የምትገኝ የተረጋጋች ሀገር መሆኗን በተጨባጭ የሚያሳይ ታላቅ አጋጣሚ ነው።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ እና ጸጋዎች በአካል የሚመለከትበት መድረክ በመሆኑ፣ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የግሉ ዘርፍ እና ሕብረተሰቡ በንቃት ሊሳተፉበት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በዚህም ኢትዮጵያ የትናንቱን በጎ ታሪክ ከዛሬው ጥረት ጋር በማስተሳሰር የተሻለ ነገን እየገነባች ትገኛለች። COP32 ጉባኤን በስኬት ማጠናቀቅ ሀገራችን በቀጣናው፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት እና ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ምዕራፍ ይሆናል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: