በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዘንድ ለዘመናት የዘለቀው የሀገር ሽማግሌዎች ሚና እና ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶች፣ ከመደበኛ የፍትሕ ተቋማት ባልተናነሰ መልኩ የማኅበረሰቡን ሰላም፣ አብሮነትና ማኅበራዊ ትስስር በማስጠበቅ ረገድ የማይተካ ድርሻ አላቸው።
እነዚህ በሀገራችን በተለያዩ ስያሜዎችና አተገባበሮች የሚንቀሳቀሱ ባህላዊ ተቋማት፣ አንድ የሚያደርጋቸው ጠንካራ የጋራ የሞራል መሠረት አላቸው። እውነት፣ ይቅርታ እና እርቅ የባህላዊ ሥርዓቶቻችን ምሰሶ ናቸው፡፡
በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች በቅርጽና በአፈጻጸም ቢለያዩም መንፈሳቸው አንድ ነው። ለአብነት ያህል የኦሮሞ ገዳና ጃርሱማ፣ የአማራ ሽምግልና፣ የጉራጌ ጆካ፣ የሲዳማ አፊኒ፣ የአፋር ማዳአ፣ የሶማሌ ኄር እንዲሁም የወላይታ አዋሳያ የዚሁ ጥበብ ማሳያዎች ናቸው።
የእነዚህ ሥርዓቶች ዋነኛ የሞራል መሠረት «አሸናፊና ተሸናፊ» ከመፍጠር ይልቅ፣ የሻከረውን ግንኙነት በመጠገን ወደ ቀደመ ሰላምና መተማመን መመለስ ነው።
በሂደቱ ውስጥ እውነትን መናገር እንደ ከፍተኛ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ግዴታ ይቆጠራል። ሀቅን መደበቅ ወይም መዋሸት እንደ ፈጣሪን ያለመፍራትና ማኅበረሰቡን እንደ መክዳት ስለሚታይ፣ በጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች እውነቱን በአደባባይ ለመግለጽ የሞራል ኃላፊነት አለባቸው።
የእነዚህ ተቋማት ዋነኛ ሞተር የሆኑት የሀገር ሽማግሌዎች፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙት በሀብት ወይም በሥልጣን ሳይሆን በሕይወት ልምዳቸው፣ በታማኝነታቸው፣ በአስተዋይነታቸውና ለፍትሕ ባላቸው ቀናኢነት ነው። ሽማግሌዎቹ ያለ ምንም ክፍያ፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሰውተው የሚያገለግሉት «ሰላም ማውረድ የመንፈስ እረፍት ነው» ከሚል ጥልቅ እምነት በመነሳት ነው።
በሽምግልና ሂደት ውስጥ ቂምን መተው፣ ይቅርታ መጠየቅና ይቅር ማለት እንደ ድክመት ሳይሆን እንደ ከፍተኛ ጀግንነትና የሞራል ብስለት ይታያሉ። እርቁ ሲፈጸምም በቃል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ቡና መጠጣት፣ ዳቦ መቁረስ ወይም በጋራ መመገብ ባሉ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓቶች በመታገዝ፣ ቂሙ ዳግም እንዳያገረሽ የሚያደርግ የማኅበረሰብ ቃል ኪዳን ይታሰራል።
ዓለም በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያካበቱት ይህ ሀገር በቀል የሰላም ግንባታ ጥበብ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። እነዚህን ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እና ከዘመናዊው የፍትሕ ሥርዓት ጋር አቀናጅቶ መጠቀም፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን ለማስፈን ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: