በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የግል አየር ትራንስፖርት አቅራቢዎች የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከግል የአየር ትራንስፖርት አቅራቢዎች ጋር በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶች ላይ እና በ2018 የሥራ ዘመን ለመስራት በታቀዱ ሥራዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ላይ በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ብቻ ተገድቦ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ በረራ፤ ወደ ሌሎች ዓለም አቀፍ በረራን ማስተናገድ የሚችሉ በክልል የሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎች መውሰድ የሚል ዕቅድ በመንግስት በኩል መያዙን እና በ2018 ለመተግበር መታቀዱም ተገልጿል።
የመቀሌ፣ የባሕርዳር እና የድሬዳዋ አየር ማረፊያዎች ዓለም አቀፍ በረራን ማስተናገድ የሚችሉ በመሆኑ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነውን ዓለም አቀፍ በረራ ወደ እነዚህ የክልል አየር ማረፊያዎች በመውሰድ ጫናው ለመቀነስ መታሰቡም ነው የተነሳው።
ሌላው የክልል ከተሞችን በአየር ትራንስፖርት እርስ በእርስ ማስተሳሰር ሲሆን፤ በ2018 የሥራ ዘመን ከክልል ከተሞች አየር ማረፊያ ወደ ሌላኛው ክልል አየር ማረፊያ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ሳያስፈልግ የሚካሄድ በረራን ለማስጀመር ታቅዷል።
በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ የአየር ትራንስፖርት አቅራቢዎች ደግሞ እያደገ በመጣው በዚህ ዘርፍ በይበልጥ ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል።
በቱሪዝም እና ማዕድን ዘርፉ የተፈጠረው መነቃቃት ለአቪዬሽን ዘርፉ በርካታ ጥቅም ይዞ የመጣ በመሆኑ፤ የግል የአየር ትራንስፖርት አቅራቢዎች ይህን ዕድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በአቬሽን ዘርፍ የተሰማሩ የግሉ ተቋማት በበኩላቸው የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ሥራቸውን በይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ማሰባቸውን ገልጸው፤ በመንግሥት በኩል የጥገና ማዕከላት እና የባንክ ብድር እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።
በሀ/ሚካኤል ክፍሉ