Search

በመቐለ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል ያጋጠሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ ነው

ዓርብ ኅዳር 18, 2019 48

የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አመራሮች ከሕብረት ሥራ ማኅበራት እና ገበያ ልማት ኤጀንሲ ጋር በመሆን በመቐለ የሚገኘውን የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት በቢሮው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ሙሉ ኃይለኪሮስ የፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻ፣ የኮርማዎች እንክብካቤ ክፍል እና ላቦራቶሪውን ለአመራሮቹ አስጎብኝተዋል።

ማዕከሉ የእንስሳትን ዝርያ ጥራት በማሻሻል ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በክልሉ መቐለን ጨምሮ በሽሬ እና በማይጨው በድምሩ ሦስት የፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻ ማዕከላት እንደሚገኙ አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በኮርማዎች መኖ እና በውኃ እጥረት እንዲሁም በቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ብልሽት ምክንያት በተሟላ አቅም ለመሥራት ፈተና እንደገጠመው አቶ ሙሉ አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ብርሃኑ ጥጋቡ ማዕከሉ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት አድንቀው፣ ያሉበትን ክፍተቶች በዝርዝር በጽሑፍ እንዲቀርቡላቸው ጠይቀዋል።

ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት ቢሮው ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

በአስማረ ብርሃኑ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: