የኢትዮጵያ ታሪክ በቀላል መንገድ የተጻፈ አይደለም። ለዘመናት የዘለቀችው በውስጥም ሆነ በውጭ በተደቀኑ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ፣ ታሪኳን እና ክብሯን አስጠብቃ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ ይህንን እውነት በግልጽ አስቀምጠዋል።
በማብራሪያቸውም “ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀችው በፈተናዎች ውስጥ አልፋ ነው። ኢትዮጵያ በተደራጁ ሠራዊቶቿ፣ የተባበረ ልብ ባላቸው ሕዝቦቿ እንዲሁም ዋጋ ለመክፈል በማይሰስቱ ልጆቿ አማካኝነት ፈተናዎችን ተሻግራ ስሟን አጽንታ ይዛለች” ብለዋል።
ይህ ማብራሪያ የኢትዮጵያን ኅልውና በማስጠበቅ ረገድ ዋና ምሰሶ የሆኑ ሦስት ቁልፍ ኃይሎችን ያመላክታል። እነሱም የተደራጁ ሠራዊቶች፣ የተባበረ ልብ ያላቸው ሕዝቦች እና ዋጋ ለመክፈል የማይሰስቱ ልጆች ናቸው።
የማንኛውም ሥርዓት ሰላም እና ደኅንነት የሚረጋገጠው በአስተማማኝ እና በተደራጀ የመከላከያ አቅም ነው።
በታሪክ ሂደት የኢትዮጵያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ከውጭ ወረራ እና ከውስጥ ሥጋቶች በመጠበቅ የኅልውናዋ መሠረት ሆኖ ቆይቷል።
ዲሲፕሊን፣ ዝግጁነት እና ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መገዛት የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት የሚለዩ መገለጫዎች ናቸው።
ፈተናዎች በበዙበት ወቅት ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ድንበር እና ኅልውና በማስጠበቅ ቀጣይነት እንዲኖር አድርጓል።
ዘመናዊ ተቋማዊ ግንባታ እና ሙያዊ ብቃት ሲታከልበት ይህ አቅም ለቀጣይ ትውልድ የበለጠ አስተማማኝ ዋስትና ይሆናል።
ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመሻገር የሕዝብ አንድነት እና የጋራ መንፈስ ወሳኝ ነው። ልዩነቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ኅልውና እና የጋራ ጥቅም ሲመጡ የተባበረ ልብ መፍጠር የመቋቋም አቅምን ያሳድጋል።
ሕዝብ በአንድነት ሲቆም ፈተናዎች ወደ አዲስ መነቃቃት እና የጋራ ግብ ሊቀየሩ ይችላሉ። ይህ ኅብረት በችግር ጊዜ መረዳዳትን፣ መደጋገፍን እና ለጋራ ዓላማ መሰለፍን ያጠናክራል።
በተለይም በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሽግግር ወቅት የሕዝብ መተማመን የለውጥ ሂደቱን ያፋጥናል።
ታሪክ የሚቀረጸው በቃላት ብቻ ሳይሆን፣ በመሥዋዕትነት ነው። ኢትዮጵያ ስሟን አጽንታ እንድትይዝ ያደረጉት ለነገ ትውልድ ሲሉ የራሳቸውን ምቾት እና ሕይወት ለመስጠት ያልተቆጠቡ ዜጎች ናቸው።
በየትኛውም ዘመን የሚነሱ ዋጋ ለመክፈል የማይሰስቱ ልጆች የጽናት እና የኢትዮጵያ ፍቅር ተምሳሌት ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ ያለፈን ታሪክ ከማስታወስ ባለፈ ለዛሬ እና ለነገ የጋራ ኃላፊነትን የሚያስገነዝብ ነው።
ዛሬም የሚገጥሙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊም ሆነ የጸጥታ ፈተናዎች በተመሳሳይ መንፈስ በጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ በሕዝብ አንድነት እና በመሥዋዕትነት ዝግጁነት ሊፈቱ እንደሚችሉ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ ማለፏ የጥንካሬዋ ማረጋገጫ ነው። ያንን ጥንካሬ አስቀጥሎ የኢትዮጵያን ስም እና ክብር ማጽናት የሁሉም ትውልድ የጋራ ኃላፊነት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: