Search

የዘመናት መለያ ተቀየረ፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብርና መሪነቱን አስረከበ

ዓርብ ኅዳር 18, 2019 39

ለአሥርት ዓመታት በመጻሕፍት እና በፖሊሲ ሰነዶች ሲስተጋባ የኖረው "የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግብርና መር ነው" የሚለው መሠረታዊ መለያ በይፋ ተቀይሯል።

ለአሥራ አንድ ዓመታት ሳይከለስ የቆየው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስሌት ሲዘምን (GDP Rebasing)፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብርና ወደ ሦስተኛ ደረጃ ወርዶ የአገልግሎት እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች የኢኮኖሚውን መሪነት ተረክበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) በጥብቅ ስሌት 210 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ይፋ አድርገዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ከደቡብ አፍሪካ እና ከናይጄሪያ ቀጥሎ ሦስተኛው፣ በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ አንደኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ሆናለች።

ይህ አዲስ ቁመና የተገኘው ከዓለም ባንክ እና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር በመተባበር ለአንድ ዓመት ተኩል በተካሄደ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ቆጠራና ክለሳ ነው።

በዓለም አቀፍ መስፈርት በየአምስት ዓመቱ መከለስ የነበረበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላለፉት 11 ዓመታት ባለመከለሱ፣ ትሪሊየኖችን የሚያንቀሳቅሱ አዳዲስ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከስሌት ውጭ ሆነው ቆይተው ነበር።

በአዲሱ ስሌት የተካተቱት ዘርፎች የኢትዮጵያን ዘመናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።

በባንኮች የዲጂታል ዋሌት 164 ሚሊየን አካውንቶች ተከፍተው 11 ትሪሊየን ብር የሚንቀሳቀስበት ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም 70 ሚሊየን ዜጎች የሚገለገሉባቸው ቴሌብር እና ኤም-ፔሳ ዋነኞቹ ናቸው።

በተጨማሪም የከተሞች የኮሪደር ልማት፣ ከ3 ወደ 15 በላይ ያደጉት ኢንዱስትሪያል ፓርኮች፣ የሌማት ትሩፋት፣ የክላስተር ግብርና፣ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ገናሌ ዳዋ ያሉ ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም የኮንፈረንስ ቱሪዝም በቆጠራው ውስጥ ተካትተዋል።

የክለሳው ትልቁ ግኝት የኢኮኖሚ ዘርፎቹ መዋቅራዊ ሽግግር (Structural Transformation) ነው። በዚህም መሠረት ግብርና ሳይቀንስ ነገር ግን ሌሎች ዘርፎች በፍጥነት በማደጋቸው የኢኮኖሚው መሠረት ሰፍቷል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት የአገልግሎት ዘርፉ በዲጂታል ፋይናንስ፣ በትራንስፖርት፣ በቱሪዝም እና በንግድ በመታገዝ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቱ 33.8 በመቶ ድርሻ በመያዝ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።

ኮንስትራክሽንን እና አምራች ዘርፉን ያካተተው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ በ14.3 በመቶ የዕድገት ትንበያ 31.8 በመቶ ድርሻ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ለዘመናት ኢኮኖሚውን ሲመራ የኖረው ግብርና በ7.7 በመቶ ጠንካራ ዕድገት እያስመዘገበ ቢሆንም በድርሻ መጠን 31.4 በመቶ በመያዝ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ወርዷል።

ይህ መዋቅራዊ ለውጥ በፋይናንስ እና በማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትም ታጅቧል። ቀደም ሲል ከአጠቃላይ ብድር ከ80 በመቶ በላዩ ወደ መንግሥት ይሄድ የነበረው አሠራር ተቀይሮ፣ ባለፉት ሦስት ወራት ከተለቀቀው 426 ቢሊየን ብር ብድር 98 በመቶው ለግሉ ዘርፍ ሲሰጥ መንግሥት የወሰደው ከ2 በመቶ ያነሰ ብቻ ነው።

በተመሳሳይ በመደበኛ እና በትይዩ የምንዛሬ ገበያ መካከል የነበረው የ110 በመቶ ልዩነት ወደ 13 በመቶ ዝቅ ብሏል።

የውጭ ምንዛሬ ክምችትም ከ20 እጥፍ በላይ ማደጉ እና የአንድ ዓመት የወጪ ንግድ ገቢ የነበረው 3.1 ቢሊየን ዶላር በአንድ ሩብ ዓመት ብቻ መገኘቱ፣ ኢትዮጵያ ከ2028 ዕቅዷ ቀድማ ከከፍተኛ የዕዳ ሥጋት ወደ መካከለኛ ደረጃ እንድትሸጋገር አስችሏታል።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: