ኢትዮጵያ በሰላማዊ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ደህንነቱ የተጠበቀ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ሀገሪቷ የእራሷ የባሕር በር ማግኘት ብትችል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው ሀገራትም ጭምር እንደሚሆን የታሪክ ተመራማሪው አደም ካሚል (ፕ/ር) ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የምግብ ዋስትና እና የውሃ ችግር ለገልፍ ሀገራት አሳሳቢ መሆኑን ያነሱት የታሪክ ተመራማሪው፤ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ብትቀርብ ምርቶቿን በቀላሉ በእራሷ ወደብ በኩል ለሀገራቱ ማቅረብ ያስችላታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የስልጣኔ መሰረት ቀይ ባህር ነው ያሉት ተመራማሪው፤ ኢትዮጵያ ወደ ነበረችበት ገናናነት እንድትመለስ ዜጎቾም ከድህነት እንዲወጡ አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በሴራ ከቀይ ባሕር እድትርቅ መደረጉን የገለጹት አደም ካሚል (ፕ/ር)፤ ከድርጊቱ ጀርባ ያሉ ሀገራት የኢትዮጵያ እድገት እና አንድነት የማይፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የህልውና ጉዳይ የሆነው የባሕር በር ለማግኘት መንግሥት በዲፕሎማሲው መስክ ከሚሰራው ሥራ ባሻገር ዜጎች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት