በአዲስ አበባ ከተማ በተሠሩ የኮሪደር ልማቶች ለአፍሪካ የነበረን ከተማ አፍርሶ ልዩ ከተማን የመገንባት ጅማሮን ያሳየንበት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ ያለውን የ8 ኪ.ሜ የኮሪደር ልማትን መመረቃቸውን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው የኮሪደር ልማት እስካሁን ካሉት የልማት ሥራዎች ከባዱ ነው ሲሉ ነው የጠቀሱት።
ለዚህ ምክንያት ደግሞ አካባቢው ብዙ ሕንፃዎች ያሉበት በመሆኑ በቀላል አፍርሶ ለመሥራት የሚያስቸግር ስፍራ በመሆኑ ነው ብለዋል።
በዚህ 8 ኪ.ሜ የኮሪደር ልማት 16 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ፣ 15 የመኪና ማቆሚያ እና የታክሲ መጫኛዎች እንዲሁም 15 ለሕዝብ የሚሆኑ መናፈሻዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
ስፍራው ብዙ ሕንፃዎች ያሉበት ቢሆንም በተገኘው ቦታ ላይ ግን ጥሩ እና በቂ ነገር መሥራት ተችሏል ብለዋል።
በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስምንት ኮሪደሮችን ለመስራት መታቀዱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዛሬው ዕለት የተመረቀው አምስተኛው ኮሪደር ልማት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ባሰብነው ልክ እና ከአንደኛው ዙር በተሻለ መልኩ አጠናቅቀናል፤ ለሕዝባችን በገባነው ቃል መሠረት ከአዲሱ ዓመት በፊት አብዛኛውን ሥራዎች ሠርተናል ሲሉም አክለዋል።
የአዲስ አበባ ሕዝብ የከተማው ባለቤት ሆኖ ከተማዋን ለመቀየር በመወሰኑ እና የከተማዋ ማማር ለእኔው ነው ብሎ በመሥራቱ ጥሩ ውጤት ማየት ችለናልም ሲሉ ተናግረዋል።
ከተማዋ ለቱሪስት አገልግሎት ምቹ፣ ለፋይናንሻል ሴክተር እና ለቴክኖሎጂ ምንጭ መሆን አለባት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኢንዱስትሪዎች እና የማዕድን ሴክተሩ ከከተማ ወጣ በማድረግ በከተማ መሐል ላይ ሆቴሎች፣ ሞሎች፣ ሆስፒታሎች ኖረው ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ እና ገቢ እንዲገኝ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን ሟሟላት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በከተማዋ የመጡት ለውጦች በቀላሉ የተሳኩ እንዳልሆኑ ጠቁመው፤ ሕዝቡ ለማደግ፣ ለመለወጥ እና የተሻለ ከባቢን ለመፍጠር የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የልማት ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም አሁንም ግን በርካታ አሮጌ መኪናዎች ስላሉ በበቂ ደረጃ አየሩ የፀዳ አይደለም፤ በዚህ ላይ ተጨማሪ ሥራዎች በሚቀጥሉት ዓመታት ይሥራል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በሐይማኖት ከበደ
#ebcdotstream #EBC #PMAbiy #corridordevelopment