ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ መፃዒ ተስፋዋ ነው ሲሉ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለፁ።
ሕዳሴ ግድብ ከኃይል ማመንጨት በዘለለ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ኢንጂነር ክፍሌ ገልፀዋል።
ግድቡ በዓመት 15 ሺህ 760 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል እንደሚያመነጭ ጠቅሰው፤ በዚህም 1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንደሚያስገኝ ነው የተናገሩት።
ከሽያጭ ከምናገኘው ገቢ በላይ ግድቡ በሀገሪቱ ልማት ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ነው ያሉት።
ለአብነትም ታዳሽ ኃይል የሚያመነጨው ፕሮጀክቱ አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች እንዲነቃቁ እና እንዲዘምኑ ያደርጋል ብለዋል።
ከኃይል አቅርቦት በተጨማሪ ግድቡ ከፍተኛ የዓሳ ምርት ክምችት እንዳለው ተናግረዋል።
በውስጡ 70 ደሴቶች ያሉትና 270 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው “ንጋት” ሐይቅ ለቱሪስት ፍሰት መጨመር ብሎም ለሆቴል እና መስተንግዶ ዘርፍ መስፋፋት አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ነው ያመላከቱት።
ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለታችኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።
ውኃው በቋሚነት የሚፈስ በመሆኑ በበጋ ወቅት የውሃ እጥረት እንዳያጋጥማቸው እንዲሁም የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ይከላከላል ብለዋል።