ኢትዮጵያን በጠንካራ መሠረት ላይ ለማፅናት በጀመርነው ተግባራዊ ሥራ ሀገራዊ ተቋሞቻችን ከፍተኛ ሚና አላቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በመሆኑም የሀገራችንን የዕድገት ጉዞ ለማስቀጠል እና ስኬታማ ለማድረግ እንደ ሚድሮክ ያሉ ተቋማት አበርክቷቸው የላቀ ነው ብለዋል።
የፅናት ቀን ብለን በሰየምነው በዛሬው ዕለት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በተሰማራባቸው ዘርፎች የሚያመርታቸውን ምርቶች እና አገልግሎቶች የሚያስቃኝ አውደርዕይ ተመልክተናል ብለዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለኢትዮጵያ በተለያዩ ፈታኝ ወቅቶች ጭምር በፅናት በመሥራት ሕዝባዊነታቸውን ካረጋገጡ እና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ልማት ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሙ ነው ሲሉ አክለዋል።
ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በምናደርገው ጉዞ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከግብርና እስከ ማኑፋክቸሪንግ፣ ከሆቴልና ቱሪዝም እስከ ማዕድን በተለያዩ ዘርፎች በስፋት በመሰማራት እያበረከተው ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ መመልከት ችለናል ብለዋል።
በደም እና በአጥንት የፀናችው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልዕልናዋ እንዲረጋገጥ የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ ልማት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ድርሻ ይይዛል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ማዕቀፉ እንደ ሀገር የፀና ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ሆኖ ፍሬውን መመልከት እንደተጀመረም ጠቁመዋል።
ሚድሮክ ባሉት 45 ኩባንያዎች ለሀገር እና ሕዝብ ከሚያበረክተው ቀጥተኛ ድጋፍ ባለፈ ምርቶቹን በቅናሽ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረቡ፣ ሌሎች ተቋማት የገበያ ትሥሥር እንዲፈጠርላቸው በር መክፈቱ እና የካበተ ልምዱን ለማሳወቅ የዛሬውን አውደርዕይ ማዘጋጀቱ በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር ነው ብለዋል።
የሀገር ዕድገት እና ብልፅግናን እውን ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ውጪ የሚታሰብ አይደለም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ዘመናትን የተሻገረ ልምድ ያላቸው ሚድሮክን መሰል ተቋማት ተሞክሯቸውን በማጋራት እና ሕዝባዊነታቸውን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን ማፅናት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
#EBCdotstream #midroc #resilience