ባለፉት 7 ዓመታት የተተገበሩ የለውጥ ሥራዎች አስተማማኝ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እንዲገነባ መሠረት ጥለዋል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
በዛሬው ዕለት የእመርታ ቀን በመላው ኢትዮጵያ እየተከበረ ይገኛል።
በቁልፍ የልማት ዘርፎች በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በገቢ አሰባሰብ እና በሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ዕድገት እየታየ ነው ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ ለውጦቹ ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የምትደርስበትን ከፍታ የሚያሳዩ እንደሆኑም ነው የገለጹት።
"የሚያስፈልገን ነገር ያለመታከት ተግተን መሥራት እና መቀጠል ብቻ ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ።
የተሟላ የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ መደረጉ በኢኮኖሚ የሚታዩ ተደራራቢ ችግሮችን በተለይም የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ መዛባት እና የአቅርቦት ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ማድረጉንም አንስተዋል።
ለእመርታ መሰረት የሚሆኑ መልካም ውጤቶች እየተመለከትን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራ የክትትል መስመር መዘርጋቱንም ነው የጠቀሱት።
"በዛሬው ዕለት የእመርታ ቀንን ስናከብር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ከመፈረሙ ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋልም" ነው ያሉት።
"የኢትዮጵያ መንኮራኩር ተነስቷል፤ እንደ ምድር ስበት ይዘው ሊያስቀሩን የሚፈልጉ ችግሮችን ሁሉ ተሻግረን፣ ፈተናዎቹን አልፈን ወደ ምንፈልገው ከፍታ እንደምንደርስ ምንም ጥርጥር የለንም" ብለዋል።
በቅርቡ ያየነው ውጤት የሩቁን እንድናረጋግጥ አድርጎናል ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በሜሮን ንብረት