በሕገ-ወጥ የወርቅ፣ የጦር መሣሪያ እና የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተሰማርተው በነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እና ኢትዮጵያውያን ላይ በአዲስ አበባ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በጥብቅ ዲሲፕሊን የመረጃ ክትትል ሲደረግ ቆይቶ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር መረጃ እና ማስረጃ ተደራጅቶ በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋሉን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ለኢቢሲ በላከው መግለጫ አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎቹ የወርቅ ማዕድን በሕገ ወጥ መንገድ በማምረት፣ በመሰወር እና በማዘዋወር፣ የሀገራችንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን እንዲሁም ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን በማዘዋወር ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ መግለጫው ጠቁሟል።
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና ከየክልሎቹ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ልዩ ኦፕሬሽን እስካሁን 45 የውጪ ሀገር ዜጎች እና 31 የሀገር ውስጥ በድምሩ 76 ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል።
ተጠርጣሪዎች ላይ በተደረገ ብርበራ በሕገ ወጥ መንገድ የተከማቹ ግምታቸው ከ7 ኪ.ግ በላይ የወርቅ ምርቶች እና ጌጣጌጥ፣ የወርቅ ማቅለጫ እና መመዘኛ መሣሪያዎች እንዲሁም አቅጣጫ ጠቋሚ ጂፒኤስ እና ማጠቢያ ኬሚካሎች ተገኝቶባቸዋል።
እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ማለትም 19,707,465 የኢትዮጵያ ብር፣ 285,797 የአሜሪካ ዶላር፣ 207,910 ዩሮ፣ 177,930 4,075 የቱርክ ሊሬ፣ 16 ድርሀምና ሌሎች የተለያዩ የውጪ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች እንዲሁም የተለያዩ ጦር መሣሪያዎች ተይዘዋል።
ለእዚሁ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ሲጠቀሙባቸው ተከማችተው የተገኙ ነዳጅ የያዙ በርካታ በርሜሎች፣ ጄነሬተሮች፣ ተሽከርካሪዎች እና የተለያዩ ሀገራት ፓስፖርቶች፣ ላኘቶፖች እና ሰነዶች በኤግዝቢትነት መያዝ መቻሉን ነው አገልግሎቱ በመግለጫው ያስታወቀው።
ይህ የወንጀል ድርጊት ሆን ተብሎ የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማዛባት እንዲሁም የዋጋ ግሽበት በማናር በማኅበረሰቡ ላይ ጫና በመፍጠር ኑሮውን ለማናጋት እና የሀገራችንን ኢኮኖሚ አደጋ ላይ ለመጣል ታቅዶ ሲሠራ እንደነበረ መግለጫው አመልክቷል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የወንጀል መረቡን ለመበጣጠስ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ተጨማሪ ክትትሎችን እና ጥናቶችን በማድረግ ኦፕሬሽኑን የቀጠለ መሆኑን ገልጾ፣
ይህንን በመረዳት ኅብረተሰቡ መሰል ሕገወጥ ድርጊቶችን በመጠቆም የተደራጁ ወንጀሎችን በመዋጋት ሂደቱ ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪውን አቅርቧል።
በተጨማሪም ሁሉም የክልል መስተዳደሮች ያለ ፌደራል መንግስት እውቅና እንዲሁም ያለ ኢሚግሬሽን ሕጋዊ የስራ ፈቃድ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ በየትኛውም አካባቢ በመሰል የስራ ዘርፍ ላይ እንዲሰማራ ጊዜያዊም ይሁን ቋሚ ፈቃድ መስጠት እንደማይቻል በመገንዘብ ይህ አይነት ሕገወጥ ተግባርን በመከታተል የወንጀል ድርጊቱን በመከላከል ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ አሳስቧል።