Search

ምሩቃን ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ለሀገር እድገትና ለዜጎች ጠቃሚነት ለማዋል ዝግጁ መሆን አለባቸው -አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

ቅዳሜ ሰኔ 20, 2018 72

የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ለሀገር እድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ለማዋል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና የዶክትሬት ድግሪ ተማሪዎች አስመርቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አገኘሁ ተሻገር፤ ኢትዮጵያ ለወጠነቻቸው ዘርፈ ብዙ የልማት እቅዶች መሳካት በእውቀትና ክህሎት የዳበረ እንዲሁም ለአዳዲስ ፈጣራዎች የተዘጋጀ የሰው ሃብት ያስፈልጋታል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ትልቅ አቅም መሆናቸውን አንስተው፤ ምሩቃን ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ለሀገር እድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ለማዋል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

2030 ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የተወጠነውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት መሪ ተዋናይ መሆን እንዳለባቸው አንስተው ለሀገር እድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት እንዲተጉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የተማሩ ወጣቶች የሀገር ግንባታ ሂደት ዋነኛ ተዋናዮች በመሆናቸው የዘውትር የህይወት ፍልስፍናቸውና መርሃቸው ስሜት ሳይሆን ስሌትና ብስለት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ ይትባረክ (/) ምሩቃን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ለሀገራዊ ዕድገትና ለማህበረሰብ ለውጥ ለማዋል ዝግጁ እንዲሆኑ አስገንዝበዋል።

በቀሰማችሁት እውቀት ማህበረሰቡን ለማገልገል የተቀበላችሁት ታላቅ አደራ በመሆኑ አደራችሁን በብቃት መወጣት ይኖርባችኋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።