ኦሮሚያ ሶቨሪን ፈንድ እና ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በግብርና፣ በማዕድን እና በሌሎች መስኮች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የፈፀሙት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀማል አሕመድ እና የኦሮሚያ ሶቨሪን ፈንድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አደሬ አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው።
ስምምነቱ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን ሀብቶች በመጠቀም መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ኢኮኖሚን ማሳደግን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጀማል አሕመድ ተናግረዋል።
በተለይ ከክልሉ መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን ሻይ ቅጠልን አምርቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አንደኛው የስምምነቱ አካል መሆኑን አንሥተዋል።
በኦሮሚያ ገጠራማ አካባቢዎች ውስጥ ያሉ ትልልቅ ልማቶችን በቀጥታ ባለሀብት ብቻ እንዲያለማ ብቻ ሳይሆን የኦሮሚያ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ ሆነው ሀብት የሚፈጥሩበትም ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ስምምነት መሆኑን የሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ሶቨሪን ፈንድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አደሬ አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ተቋማቱ ያላቸውን ሀብት ተጠቅመው በጋራ በመሥራት የተስማሙባቸውን ዘርፎች ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በስምምነቱ መድረክ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ ተቋማቱ በጋራ ሠርተው የሚያመርቷቸውን ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንዳለባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል።
በብሩክታዊት አሥራት
#EBC #ebcdotstream #MIDROC #investment