Search

የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ በ2030 ዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

ሓሙስ መስከረም 01, 2018 90

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ5 ዓመታት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር መታቀዱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን ትልቅ እመርታ ላይ የሚያደርስ መሆኑንም ነው አቶ መስፍን የ2018 የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተናገሩት።

አየር መንገዱ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን በማስፋፋትና አዳዲስ የበረራ መስመሮችን በመክፈት በከፍታ ላይ መሆኑን በመጥቀስ፤ በ2018 በጀት ዓመት የአዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ተነሺ አርሶ አደሮችን ወደ አዲስ ቦታ ለማዘዋወር የቤቶች ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን በመግለጽ፤ ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታም ፋይናንስ እያፈላለግን ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያው እጅግ ዘመናዊ ተርሚናል ያለውና ከዓለም ታላላቅ አውሮፕላን ማረፊያዎች ተርታ እንደሚሰለፍ በመጥቀስ፤ አየር መንገዱን ከዓለም ስመ ገናናዎች አንዱ ያደርገዋል ብለዋል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሥራ ሲጀምር የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕን ማረፊያም እጅግ ዘምኖ የሀገር ውስጥ በረራን በዓለም አቀፍ የአገልግሎት ደረጃ እንዲሰጥ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

አዲሱ ዓመት ለመላው ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለአየር መንገዱ ደንበኞችና ሠራተኞች የደስታ፣ የፍቅርና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

#EBCdotstream #NewYear #EthiopianNewYear #2018EC #EAL #EthiopianAirlines