Search

የኢትዮጵያ ትርክት አሁን ከሕዳሴ ግድብ በፊት እና በኋላ ተብሎ መከፈል የሚችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ሰኞ መስከረም 05, 2018 65

የኢትዮጵያ ስንክሳር ከሁለቱ ውሀዎች  ከዓባይ ወንዝና ከቀይ ባህር ጋር የሚያያዝ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገልጸዋል።

ከ17ኛው ክፍለ ዘመን የቅኝ ገዢዎች አፍሪካን የመቀራመት ተግባር ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥታት ዓባይን ለተለያየ ጥቅም የማዋል የሀገሪቱን ተፈጥሯዊ መብት ለማስጠበቅ ሲታገሉ እንደነበር ተናግረዋል።

ዲያቆን ዳንኤል ከኢቢሲ ኤፍ ኤም ኢዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ እንድትሆን መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ ህዝቡ እና ልሒቃንም ሲሞግቱ ኖረዋል።

ቅኝ ገዢዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያን ከዓባይ ውጭ ለማድረግ ብዙ ለፍተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታቸውን መልሰው ያገኙበት ታሪካዊ ድል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ትርክት አሁን ከሕዳሴ ግድብ በፊት እና በኋላ ተብሎ መከፈል የሚችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

ከግድቡ በፊት እኛም አንችልም ብለን፣ ሌሎችም አትችሉም ብለውን፤ የዓለም የገንዘብ ተቋማት ካልደገፉን መሥራት አንችልም በሚል ትርክት ታስረን ነበር ሲሉ ያስረዳሉ።

ከሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ ግን እኛም እንችላለን ብለን፣ እነርሱም ትችላላችሁ ያሉበት፤ በራሳችን አቅም የምንፈልገውን ፖሊሲ መፈጸም እንዲሁም በራሳችን ጉዳይ ራሳችን መወሰን እንደምንችል እና ለዚህም የማንንም ፈቃድ መጠየቅ እንደማይገባን ትርክት የገነባንበት ነው ብለዋል።

ዲያቆን ዳንኤል እንደሚሉት፥ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትጠቀም  ለማድረግ የሚሰነዘሩ ጫናዎች የጥቁር ሕዝብ አካል በመሆኗም ጭምር የመጡ ናቸው።

ጥቁሮች ለመልማት የሌላ አካል ፈቃድ እና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል የሚል ትርክት ሰፍኖ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህን በጥቁር ሕዝቦች ላይ የተጫነ  የአይችሉም ትርክት ለመቀየር ኢትዮጵያ እንደ ዓድዋ ባሉ ተምሳሌታዊ  ድሎች ስትቀለብስ መኖሯን ሚኒስትሩ አውስተዋል።

አሁን የታላቁ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እንደ ፓንአፍሪካኒስት ሀገር የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦችን የመቻል አቅም ያሳየ እና አዲስ ትርክት የፈጠረ መሆኑን ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናግረዋል።

በቤተልሔም ገረመው

#GERD #Ethiopia #EBCdotstream