በሀገራችን፣ ኢትዮጵያ የሚፈጠሩት ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ምንጫቸው ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፣ ለዚሁ ጉዳይ ትኩርት በመስጠት በሀገራችን የተከሰቱ ጦርነቶች መንሥኤዎች እና መፍትሔዎች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የሚስተዋሉ ተደጋጋሚ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ድንገቴ ክስተቶች ሳይሆኑ፣ ምንጫቸው ካለፈው የፖለቲካ ሥርዓት አወቃቀር የሚመነጭ ‘ሥርዓት-ወለድ’ ቀውሶች ናቸው።
እነዚህ ችግሮች የሚባባሱት ደግሞ፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን እንደ ግብዓት በሚጠቀም እና ልዩነትን አጉልተው በሚያሳዩ ፕሮፓጋንዳዎች ነው።
ይህ መዋቅራዊ ብልሽት ሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዳታገኝ አድርጎ በአዙሪት ውስጥ እንድትቆይ እያደረጋት ይገኛል።
የሥርዓት-ወለድ ልዩነቶች በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሱት ዋነኛ ጉዳት በዜጎች ሥነ-ልቦና ውስጥ የፈጠሩት “መንታ ማንነት” ነው።
የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አተገባበር በራሱ በጎ ገጽታዎች ቢኖሩትም፣ ከሀገራዊ አንድነት ይልቅ የክልላዊ ማንነት ትርክት እንዲያይል በመደረጉ ዜጎች በጋራ ማንነት እና በልዩነት መካከል እንዲዋልሉ አድርጓል።
ይህም በታሪክ አረዳድ፣ በሥልጣን ክፍፍል እና በመንግሥት አወቃቀር ላይ መሠረታዊ መቃቃሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።
ይህ ሁኔታ ታዲያ ኢትዮጵያን ዘወትር በገደል አፋፍ ላይ እንድትቆም ከማድረጋቸውም በላይ፣ እንደ ሰሜኑ ጦርነት ያሉ መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችም የዚሁ መዋቅራዊ ችግር መገለጫዎች ሆነው አልፈዋል።
የመደመር መንግሥት ይህንን ‘ሥርዓት-ወለድ’ ስብራት ለመጠገን ዋነኛው መፍትሔ የኃይል እርምጃ ሳይሆን የሐሳብ የበላይነት መሆኑን አምኖ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።
ግጭቶች እና ጦርነቶች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መቆም እንዳለባቸው በማመን፣ የቂም በቀልን አዙሪት ለመስበር “ይበቃናል” የሚል ቁርጠኝነትን አንግቧል ነው ያሉት።
በዚህም መሠረት የፖለቲካ ልዩነቶችን በጠመንጃ ሳይሆን በውይይት እና በመቀራረብ ለመፍታት የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ነው ብለዋል።
ይህንን ራዕይ ወደ ተግባር ለመቀየርም ሁሉን አቀፍ የሆነው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመው፣ ምንም እንኳን በተወሰኑ አካባቢዎች በፅንፈኛ ኃይሎች እንቅፋት ቢገጥመውም፣ በአንፃሩ እስካሁን አመርቂ ሥራ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በአጠቃላይ አሁን ላጋጠሙን ችግሮች መፍትሔው የሚገኘው በምርጫ ወይም በፍትሕ አካላት ውሳኔ ብቻ ሳይሆን፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚስማማበት የጋራ ሥርዓት እና ሕግ ሲገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስምረውበታል።
ለዘመናት ለቆዩ የታሪክ ቅሬታዎች ስለመኖራቸው እውቅና ሰጥቶ መፍታት እና በኅብረ-ብሔራዊነት ላይ የጸና አንድነትን መፍጠር የግድ ይላል።
ይህ ትውልድ ኃላፊነት ወስዶ ሥርዓታዊ ብልሽቶቹን ካላረመ፣ ችግሩ መልኩን እየቀያየረ ለልጅ ልጆች መትረፉ አይቀሬ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስጠነቀቁት።
በመሆኑም ዘላቂው መፍትሔ ልዩነቶችን እንደ ተፈጥሯዊ ጸጋ በመቀበል፣ በጋራ ሀገራዊ ማንነት ጥላ ሥር መመካከር እና ለጦርነት የሚገፋፉ ትርክቶችን በውይይት ባህል መተካት ነው።
በዮናስ በድሉ
#Ethiopia #narrative #politicalculture #nationaldialogue #EBC #ebcdotstream