ጉምሩክ ኮሚሽን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና አካባቢዎች የተውጣጡ ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሰልጥኖ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፥ ተመራቂዎቹ ሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በመከላከል የኢትዮጵያን ልማት ማፋጠንና ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ላይ በርትተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ አሰራሩን ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስልጠናው የሪፎርሙ አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በሁሉም አካባቢዎች ተሰማርቶ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት የየአካባቢውን ወግ እና ባህል በአግባቡ በሚያውቁ ብቁ የጉምሩክ ባለሙያዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ እንዲችል ሰልጣኞቹ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ነው ያሉት።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ፥ ሰልጣኞቹ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ እንዲያሳካ ከመሥራት ባለፈ የሀገሪቱን አቅም በማሳደግ ምሳሌ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በብሩክታዊት አስራት
#EBCdotstream #customs #ECC #AAU