Search

“እኛ ትምህርት ቤት ትልቅ ውጤት መጣ ሲባል ውጤቱ የተማሪ ሃይማኖት ዮናስ ስለመሆኑ እርግጠኞች ነበርን” - ብሥራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት

ሰኞ መስከረም 05, 2018 49

የብሥራተ ገብርኤል ትምህርት ቤቶች ካስፈተናቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ተማሪ ሃይማኖት ዮናስ በተፈጥሮ ሳይንስ 579/600 በማግኘት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2ኛውን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች።

የብሥራተ ገብርኤል ትምህርት ቤቶች አካዳሚክ ማናጀር አቶ ዘላለም ደምሴ ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለፁት፥ ሃይማኖት ከታች ጀምሮ እጅግ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች፣ ከአጠቃላይ ክፍሎች 1ኛ ወጥታ ዋንጫ እየተሸለመች 12ኛ ክፍል የደረሰች ናት።

ውጤቱ በድንገት ያመጣችው ሳይሆን አስቀድማ አቅዳ እና በቂ ዝግጅት አድርጋ ያሳካችው እንደሆነ ገልጸው፤ በሀገር አቀፍ ፈተናው ከፍተኛ ውጤት ለማምጣትም ቃል ገብታ እንደነበር አስታውሰዋል።

ተማሪ ሃይማኖት በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀች ጭምር እንደሆነች የገለጹት አቶ ዘላለም፤ ይህ ውጤት ለእርሷ አዲስ እንዳልሆነ እና እንደሚገባት ተናግረዋል።

"እኛ ትምህርት ቤት ትልቅ ውጤት መጣ ሲባል ውጤቱ የተማሪ ሃይማኖት ዮናስ ስለመሆኑ እርግጠኞች ነበርን" በማለት ነው በእርሷ ምን ያህል እንደሚተማመኑ የገለጹት።

ሃይማኖት ሁልጊዜ የምታጠና፣ በራሷ የምትተማመን፣ ያላትን ዕውቀት ለሌሎች የምታጋራ ብሩህ ተማሪ እንደሆነች አቶ ዘላለም አክለዋል።

በላሉ ኢታላ

#Education #MoE #12thgrade #topscore #EBCdotstream