የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን ውጤታማ ለማድረግ ተሠርቷል ሲሉ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞች እና ጥራት ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዮሐንስ ወጋሶ (ዶ/ር) ገለጹ።
ከ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አፈፃፀም ልምድ በመውሰድ ለዘንድሮው ዓመት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ስለመከናወናቸውም ነው ዶ/ር ዮሐንስ ከኢቲቪ አዲስ ቀን የሀገር ጉዳይ መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ የገለጹት።
የማስተማሪያ መፃሕፍት ሕትመት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የትምህርት ቤቶች እድሳት እና ግንባታ እንደተጠናቀቀ ተናግረዋል።
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ከ20 ሚሊዮን በላይ የ1ኛ ደረጃ መፃሕፍት ለትምህርት ቤቶቹ እንደሚሰራጩም ነው የገለጹት።
የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትን ጨምሮ ተማሪዎች መሠረታዊ ክህሎቶችን እንዲገበዩ የሚያስችሉ ውጤት ተኮር ሥራዎች እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት አሰጣጥን ቀድሞ ከነበረው ለማሻሻል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ስለመደረጉም አንስተዋል።
ባለፈው ዓመት ከ7.6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በተያዘው ዓመትም መርሐ-ግብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቶ የ2018 ዓ.ም ትምህርት በዛሬው ዕለት መጀመሩ ይታወቃል።
በሜሮን ንብረት
#MoE #Education #Preparation #EBCdotstream