Search

"ሕዳሴ ግድብ አባቶች እንዳሳኩት የዓድዋ ድል ሁሉ በዚህ ዘመን የተሳካ ዳግማዊ ዓድዋ ነው" ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

ማክሰኞ መስከረም 06, 2018 45

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ በባሕር ዳር ከተማ የድጋፍ እና የደስታ መግለጫ ሰልፍ ተካሄዷል።
በድጋፉ እና የደስታ መግለጫው ሰልፍ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዛሬ ኢትዮጵያ ሀገራችን የልማት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተሰጣትን ሀብት በራሷ አቅም፣ በራሷ ሀብት፣ ፈተናዎችን ተቋቁማ፣ ለአፍሪካ ምሳሌ በሚኾን መልኩ አጠናቃለች ነው ያሉት።
ሕዳሴ ግድቡ አባቶች እንዳሳኩት የዓድዋ ድል ሁሉ በዚህ ዘመን የተሳካ ዳግማዊ ዓድዋ መኾኑን ገልጸዋል።
እነኾ ጠላቶች የጠነሰሱትን ጥሰን እና በጣጥሰን ይሄው በአንድነት ቆመናል፤ ዛሬም በፍጹም አርበኝነት አሸንፍናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ጫናውን ተቋቁማ፣ የሕዝቦቿን አንድነት እና አይበገሬነት ተጠቅማ ድል ማድረጓን ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊያን እንደ ዓድዋ ሁሉ ዓመላቸውን በጉያቸው፣ ስንቃቸውን በአህያቸው አድርገው በአንድነት የገነቡት፣ ለትውልድ የሚበቃ የዘመኑ ሕያው መገለጫ ኾኖ ተጠናቅቋል ነው ያሉት።
የሕዳሴ መጠናቀቅ ሉዓላዊ ሀገራት ሁሉ የራሳቸውን ሀብት ማንንም ሳይጠይቁ መጠቀም እንደሚችሉ ያሳየ መኾኑን ተናግረዋል። ሕዳሴ የቅኝ ግዛትን ውል እስከመርዙ የፈወሰ፣ የራሳችን ሀብት የተጠቀምንበት ነው ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝም ተናግረዋል። የሕዳሴ ግድብ ታላቅ አቅም ያለው እና በአፍሪካ ግዙፉ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕዳሴ በጭስ ውስጥ ለኖሩ እናቶች የደረሰ እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታላቅ አቅም እንደኾነም ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት የሚበቃ፣ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር፣ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬን የሚያመጣ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ተደማጭነቷ ከፍ እንዲል የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ቅቡልነት ያሻሻለ፣ ከፈጣሪ የተሰጠን፣ በሕዝባችን አበርክቶ የተገኘ ክብርና እና ኩራት መኾኑንም ገልጸዋል።
ሕዳሴ ብሥራትን ይዞ መምጣቱንም አንስተዋል። በሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ማብሰሪያ ላይ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ይፋ መደረጋቸውንም ገልጸዋል። ይህም ለሕዝብ ታላቅ ተስፋ መኾኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እየሠራች መኾኗን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ነገር ግን የግጭት አዙሪት ሕዝብን እየበላ፣ ሀገርን እያዳከመ መኾኑን አንስተዋል። ይህ የግጭት አዙሪት ችግርን በውይይት የመፍታት ልምድ ማነስ የመጣ ነው ብለዋል። ግጭት የሕዝብን ኑሮ እያናጋ መኾኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ኖሯት ሳለ፣ እንደ ቁልቋል የሚያደማት ግጭት እያጋጠማት መኾኗን አንስተዋል።
መላው ኢትዮጵያውያን ከዚህ የግጭት ልምምድ እና አዙሪት ወጥተን፣ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት የኾነችው ሀገራችንን ታሪክ እና ከፍታ በሚመጥን መልኩ ልማት እና ብልጽግናን እንዲረጋገጥ፣ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችሁን እንድትወጡ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።