ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለመጨረስ የተከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ ነው፤ በብዙ ፈተናዎች አልፈን ችለን አሳይተናል ሲሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ህዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ አካሂዷል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ እንደገለጹት፤ ከዘመናት ቁጭት በኋላ በዚህ ዘመን ትውልድ በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊውን በጋራ ከቆሙ ማሳካት የማይችሉት ነገር እንደሌለ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡
የጎንደር ከተማ ሕዝብም የሕዳሴ ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የተጠናከረ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ግዮንን የሚሸኙት ሳይሆን አብረው የሚኖሩት እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጭነት ታላቁ ግዮን ወንዝ የሚሸኙት ሳይሆን አብረው የሚባጁበት፣ አብረው የሚኖሩት እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡