Search

ከ7ቱ የጉባ ብስራቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፉ የቢሾፍቱ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ማሳያ ዛሬ ተጀመረ

ማክሰኞ መስከረም 06, 2018 36

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ ለማስገንባት ያቀደውን ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ የግንባታ ፕሮጀክት ማሳያ በዛሬው ዕለት አስጀምሯል።
የግንባታውን መዋቅር፣ የፋይናንስ ስትራቴጂ፣ የአደጋ ስጋት ምላሽ አሰጣጥ ማዕቀፎችን እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ ሚናዎችን ለፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች ለማስገንዘብ ያለመ የሁለት ቀናት የፕሮጀክት ማሳያ ተካሂዷል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በ2016 ዓ.ም ወደ 20 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገዱን አንስተው የደንበኞች መጠኑም በየዓመቱ ከ10 እስከ 15 በመቶ እያደገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም ሳቢያ አየር ማረፊያው ተደጋጋሚ የማስፋፊያ ስራዎች ቢሰሩለትም ከሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በኋላ አየር ማረፊያው ከአቅሙ በላይ መንገደኞችን ለመቀበል ይገደዳል ብለዋል።
አዲስ የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በአፍሪካ ካሉ አየር ማረፊያዎች ግዙፍ ከመሆኑ ባሻገር በየግዜው እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች አቅም የሚያስተናግድ ነውም ሲሉ ተናግረዋል።
 
የገንዘብ ሚንስትሩ አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ የሚገነባው አየር ማረፊያ የሚቀጥለውን ትውልድ የሚመጥን እንደሆነ የተናገሩት የኢትዮጵያን እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ የመሸከም አቅም ያለው እንደሆነ አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ እድገት ላይ ያላትን እምነት እንደሚያሳይ የገንዘብ ሚንስትሩ ተናግረዋል።
አዲስ የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከቦሌ አየር ማረፊያ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገነባ ተገልጿል።
በመድረኩ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የገንዘብ ሚኒስተር አቶ አሕመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና የአየር መንገዱ ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ እንዲሁም ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች፣ ኮንትራክተሮች፣ እቃ አቅራቢዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።
 
በሳምሶን ገድሉ