ተማሪ ገነት መርጋ ጊሹ በ2017 ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ 579 ከ 600 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ተማሪ ነች፡፡
ተማሪ ገነት በእንግሊዘኛ 95፣ በሒሳብ 100፣ በኬሚስትሪ 93፣ በፊዚክስ 100፣ በባዮሎጂ 98 እንዲሁም በአፕቲትዩድ 93 በድምሩ 579 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ሁለት ሴቶች መካከልም አንዷ ሆናለች፡፡
ተማሪ ገነት በኦሮሚያ ክልል የዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን፤ በሀገር አቀፍ ፈተናው ከተማሪ ሃይማኖት ዮናስ ጋር እኩል 579 ነጥብ ማምጣት ችላለች፡፡
የዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዴቱ ዲቢ በተለይም ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለፁት ተማሪዋ በትምህርቷ ጎበዝና መልካም ባህሪ ያላት ናት፡፡
ተማሪ ገነት የትምህርት እና የመምህራኖች እገዛ ላይ የራሷን ጥረት ተጠቅማ ይህን ውጤት ማምጣት መቻሏንም ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለተማሪዎች ምቹ የማንበቢያ ቦታዎችና ፋሲሊቲዎች በመሟላታቸው የንባብ ባህል እንዲፈጠር ማስቻሉን ያነሱት ርዕሰ መምህሩ፤ ይህም ለውጤቱ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
በላሉ ኢታላ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #education