"ሕደሴን ማን ሠራው?"፣ "የማን ድርሻ ምን ያክል ነው?" የሚሉት ጥያቄዎች መነሳት የጀመሩት ግድቡ በመጠናቀቁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የበሰለ ፍሬ ባለቤቱ ስለሚበዛ ነው እንጂ ግድቡ ባይጠናቀቅ ትርክቱ ሌላ እንደነበር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ "አሳብበን ብንተወው ኖሮ አይ እነ እንትና አበላሹት፤ ይባላል እንጂ አንድም ሰው አይጠጋጋም ነበር" በማለት ነው ሰዎች ድል ለመጋራት እንደሚሽቀዳደሙ የገለጹት።
አሁን ግን በመሳካቱ፣ የስኬት ባለቤቱም ብዙ ስለሆነ ሁሉም የግድቡን ባለቤትነት ለመሻመት እየተሸቀዳደመ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት ስኬትን ለመሻማት ጊዜ ስለሌለው፤ የተጠናቀቀውን ነገር "የእናንተ ይሁን" በማለት ወደ ቀጣዩ ሥራ እንደሚሄድም ጠቅሰዋል።
የመደመር መንግሥት ግቡ ማሳካት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ማሳካትን ግን ብቻዬን እችላለሁ ብሎ አያምንም ብለዋል።
በዚህ እሳቤ መሰረት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መላ ኢትዮጵያውያን ገድል እና ድል እንጂ የአንድ መንግሥት ወይም የአንድ ግለሰብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ