የመደመር መንግሥት ማጠንጠኛ አራት "መ"ዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣ "መነሻ" የሚለው ቃል "ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት ሆና ሳለች ለምን ድህነት መገለጫዋ ሆነ?" የሚለው ጥያቄ ላይ የሚያጠነጥን እንደሆነ ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ ለምን ደሃ ሆነች የሚል?" ጥያቄ በመጠየቅ ወደ መነሻ በመመለስ፤ ኢትዮጵያ የመጣችበትን መንገድ ተመልክቶ ለስብራቷ መፍትሔ ማመንጨት የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ዓላማ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይህ ጥያቄ ለኢትዮጵያ የሚጠየቀው በዓለም ደሃ የሆኑ ሀገራት ስለሌሉ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ሁሉ እያላት በድህነት መኖሯ የሚያስቆጭ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በረጅም ጊዜ ውስጥ ቢለካ ኢትዮጵያ ጀግንነታቸው ያልነጠፈ ሕዝቦች መኖሪያ መሆኗ፤ ሕዝቧ ለፈጣሪ የቀረበ፣ አኩሪ የነጻነት ገድል እና ታሪክ ያለው፣ በተፈጥሮ የታደለ፤ በኪነ-ሕንጻ፣ በባህል ሀብታም የሆነ ሕዝብ እንዴት ደሃ ሆነ? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

"እርሻን የጀመረ እና ያስጀመረ ሕዝብ እንዴት ምግብ እንቆቅልሽ ሆነበት? ሸማን ሠርቶ ሲለብስ የነበረ እና ሽመናን በታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም የሚታወቅበት ሕዝብ እንዴት ልብሱን ማምረት አቅቶት ከውጭ የሚሸምት ሆነ? መድኃኒት ቀምማ ስትፈውስ የኖረችው ኢትዮጵያ እንዴት መድኃኒት ማምረት ብርቋ ሆነ?" የሚሉት ጥያቄዎች ወደ መነሻ የሚመልሱን መሆናቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
በዓለም ላይ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ያላቸው ሀገራት ወርቅ የሚያከማቹት በማምረት ሳይሆን ከእኛ በመግዛት እንደሆነ ጠቅሰው፣ እኛ ግን የበዛውን ወርቅ በከርሰ ምድር አስቀምጠን ደሃ የተባልነው ባስቀመጥንበት ቦታ ልዩነት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።
ያስቀመጥንበት ቦታ ደሃ የሚያስብለን ከሆነ የማሰብ ኃይላችንን ተጠቅመን የቦታ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመው፣ የተሰጠንን ድህነት ተቀብለን መቀመጥ ሳይሆን የቦታ ለውጥ አድርገን ከድህነት ለመውጣት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በለሚ ታደሰ