ኢትዮጵያ ሰላምን ታስቀድማለች፤ ድህነትን ትፋለማለች፤ መውጫ፣ መግቢያ በሯን ታበጃለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ወንድም እህቶቻችንም ይህ አይቀሬ መንገድ መሆኑን ተገንዝበው በፈጠነ ጊዜ ለድርድር ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያን የምታክል ሀገር በሯ ተዘግቶ ለልጆቻችን መተላለፍ አለባት ብሎ ማመን ተገቢ እሳቤ አይደለም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር።
የኛ የሆነውን ቀይ ባህርን መልሶ ለመጠየቅ የሚሰጋ፣ የሚጠራጠር ትውልድ መፈጠሩ የሥነ ልቦና ስብራት አካል መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና ለዘለዓለም ትኖራለች ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ካለ እርሱ የሞተ ነው ብለዋል።
የቀይ ባህርን ጉዳይ ይህ ትውልድ አይችለውም ብለው የሚያስቡ አሉ፤ እኔ ግን ኢትዮጵያ እንደምትችል አረጋግጥላችኋለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
ይህን በምሳሌ ሲያስረዱም፥ የዛሬ 155 ዓመት ስዊዝ ካናልን በጀግኖች ልጆቻቸው ያሳኩ ሰዎች ዛሬ እፎይ ብለው በዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር ያገኛሉ፤ ስዊዝ ካናል ሲሰራ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ ወይም ናይጄሪያ ውስጥ የሞቱ ሰዎች ነበሩ፣ ግን ታሪክ የላቸውም፤ ስዊዝ ካናልን እየሰሩ በሐሩር፣ በምግብና በመድኃኒት እጥረት የሞቱ ሰዎች ግን ዛሬም ድረስ ታሪካቸው ሕያው ነው ብለዋል።
ከእኔ እና ከናንተ መካከል ዘለዓለማዊ የሆነ፣ የማይሞት አንድም ሰው የለም፣ እኔም እናንተም ሟቾች ነን፤ ታሪክ ሰርቶ የሞተ ሰው ግን ስሙ በትውልድ መካከል ሲተላለፍ ይኖራል ነው ያሉት።
የቀይ ባህርን ጉዳይ ለማሳካት ግጭት ውይም ውጊያ ያስፈልጋል ብለን አናምንም፣ ለዚህም ነው ለ5 ዓመታት ስንለማመጥ የኖርነው፤ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የተዘጋባትን በር ለማስከፈት እና ድሃ ያስባላትን መጠሪያ ለመፋቅ ትግሏን ትቀጥላለች ብለዋል።
በዚህ ዙሪያ በየትኛውም መድረክ ከኢትዮጵያ ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር የሚፈቅድ አካል ካለ ከምን ጊዜውም በላይ እጃችን የተዘረጋ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ
#EBCdotstream #YemedemerMengist #PMAbiyAhmed