ጫካ ፕሮጀክት ትልቅ ከተማ እንጂ እንደሚባለው ቤተመንግሥት እንዳልሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት መጽሐፍን አስመልክቶ የዳሰሳ ሐሳብ ያቀረቡት አቶ ጌታቸው፣ "እኔም እንደ ሌሎች ሰዎች ቤተመንግሥት እየሠሩ ነው ብዬ በማመን ‘ምን አለ ሌላ ሕዝብ የሚጠቅም ፕሮጀክት ቢሠሩበት?’ ብያለሁ በማለት ስለ ፕሮጀክቱ የነበራቸውን እሳቤ አጋርተዋል።
ሄደው ያዩት ግን ቤተመንግሥትን ሳይሆን ትልቅ ከተማ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሥራው ሌሎች እስኪፀዱ ድረስ ከመጠበቅ አዳዲስ ነገሮችን መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።
በገባኝ መጠን ሌሎች ትልልቅ ሀገራት ከደረሱበት ተጀምሮ እየተሠራ ነው የሚል ዕምነት አለኝ ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ይህን ለማድረግ ማቀድ፣ መፍጠር እና መፍጠን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
የኔ ምክር ይህ ፍጥነት እዚህ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም የሚል ነው በማለት መልካም ተሞክሮው መስፋት እንዳለበት መልዕክት አክለዋል።
የሕልም ተጋሪዎችን ማብዛት፣ አስተሳሰቡን ወደ ታች ማውረድ እና ሕዝብን እኩል ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችል መልኩ መሥራትም ወሳኝ መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ያዩአቸው አዳዲስ ሕንጻዎች ከፍተኛ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል እየተፈጠረ መሆኑን የተረዱባቸው እንደሆነ ጠቅሰው፣ በሀገራችን እንደዚህ ዓይነት ጥራት ያላቸው ህንጻዎች ይሠራሉ ብለው አስበው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
እንደነዚህ ዓይነት መልካም ማሳያዎች አዲስ አበባን እንደመነሻ አድርገው ወደ ክልሎችም መውረድ እንዳለባቸቸው ጠቅሰዋል።
#EBC #ebcdotstream #AbiyAhmedAli #YemedemerMengist