Search

በኅብረቱ ዓባይን ገርቶ ለልማት ያዋለው ሕዝብ የኢትዮጵያን ማንሠራራት ለማሳካት አይሳነውም፦ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

ሓሙስ መስከረም 08, 2018 85

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝብ ከጥሪቱ እስከ ሕይወቱ መስዋዕትነት ከፍሎ የገነባው የአዲሱ ትውልድ አሻራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

በዚህም አይቻልም የሚለው አስተሳሰብ መሰበሩን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የተናገሩት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል የተካሄደውን ሕዝባዊ የድጋፍ ሰከልፍ አስመልክቶ ርዕሰ መስተዳድሩ ባስለላለፉት መልዕክት፤ ሕዳሴ ግድብ የአሁኑ ትውልድ በላቡ እና በደሙ ጠብታ ባኖረው አሻራ ዳግማዊ ዓድዋን እውን ያደረገበት ነው ብለዋል

ግድቡ ከውጭ እና ከውስጥ የተቃጡበትን ፈተናዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ብቁ አመራር እና በሕዝብ መስዋዕትነት አልፎ ለፍጻሜ መብቃቱንም ጠቅሰዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ የምሥራቅ አፍሪካን እና የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን የውኃ ፖለቲካ የቀየረ እንደሆነ አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

ይህ በሕዝብ ኅበረት እና መስዋዕትነት የተገኘው ድል ለሀገር ፍቅር በሚከፈለው መስዋዕትነት የተገኘ እና ሁሌም የሚታሰብ ነው ብለዋል።

"እንኳን በኅበረት ዘምተን ድል አስመዘገብን! ይህን እውን ላደረጋችሁ የሀገራችን ሕዝቦች ምሥጋና ይገባችኋል! ክበሩ!" በማለት ሕዝቡን አመስግነዋል።

ሕዝቡ ከሰሜን አስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ወጥቶ በግድቡ መጠናቀቅ ደስታውን በመግለጽ ለወዳጅም ለጠላትም መልዕክቱን አስተላልፏል ብለዋል አቶ ሽመልስ።

የኢትዮጵያን ትንሣኤ ማየትም መስማትም የማይፈልጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ምኞት ሕዝቡ ባሳየው አንድነት መምከኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።

ሕዝቡ በጎጥ እና በጎሳ ሳይከፋፈል በአንድነት ይህን ታላቅ ታሪክ በመሥራቱ የኦርሚያ ክልል መንግሥት የላቀ ምሥጋና ያቀርባል ብለዋል አቶ ሽመልስ።

ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ምዕራፍ አዲስ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሽመልስ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉባ ላይ የሕዳሴ ግድብን ሪቫን ከቆረጡ በኋላ ያበሰሯቸውን የኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን ፕሮጀክቶችን በአንድንነት በመፈጸም ድህነት ላይ የተከፈተውን ዘመቻ በድል ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ዓላማ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እና ለአፍሪካ ሰላም መሥራት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህን ዓላማ ለማሳካትም ቀን እና ሌሊት እንሠራለን ብለዋል።

በኅብረቱ ዓባይን ገርቶ ለልማት ያዋለው ሕዝብ የኢትዮጵያን ማንሠራራት ለማሳካት እንደማይሳነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በለሚ ታደሰ