ሰባቱን የጉባ ብስራቶች በአጭር ጊዜ በመፈፀም ሶስተኛው ዓድዋችንን እንደግማለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ዳግማዊ ዓድዋ የሆነውን ሕዳሴ እውን ለማድረግ፤ ኢትዮጵያውያን የከፈሉት ዋጋ ታላቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተን በአንድ ልብ ከሠራን 3ኛው ዓድዋችን በቅርቡ እውን ይሆናል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በዓድዋ ጊዜ በአንድነት ታሪክ ሰርተናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ 2ኛው ዓድዋችን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፥ በፈተናዎች መካከል በተባበረ ክንድ እውን መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ጊዜው ለ3ኛ ዓድዋ የምንዘጋጅበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በዓድዋ ጊዜ እንደነበረው ሁሉ አንድ ከሆንን ሀገር በመለወጥ ሌላ ታሪክ በአጭር ጊዜ መስራት እንችላለን ብለዋል።
ይህንን ለማሳካት በአንድነት ተግቶ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በተመስገን ተስፋዬ