Search

የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በታቀደው መሠረት እንዲከናወን ድርሻውን ተውጥቷል - ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)

ሓሙስ መስከረም 08, 2018 30

የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በታቀደው መሠረት እንዲከናወን ድርሻውን መወጣቱን የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(/) ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የባለፈው የክረምት ወቅት ትንበያ ግምገማ እና የመጪው በጋ ወቅት ትንበያ ይፋ የሚያደርግበት መድረክ እየተካሄደ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎች መሠረት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን መቀነስ መቻሉንም ነው ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ የጠቀሱት።

በቅርብ ዓመታት በሚቲዎሮሎጂ ተቋማት ላይ በተሠራ ሥራ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን መቀነስ መቻሉንም ተናግረዋል።

በዚህም ዜጎችን ከጎርፍ አደጋ መታደግ መቻሉን አንስተዋል።

አሁን ላይ የአየር ጠባይ ትንበያ ቴክኖሎጂ ሽፋንም 63 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩትያለፈው ክረምት ወቅት ትንበያ መሬት ላይ ካለው ጋር የተጣጣመ እንደነበር ተገልጿል።

የቀጣይ የበጋ ወቅት ትንበያ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና የደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አከባቢዎች፤ መደበኛና ከመደበኛ በታች የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (/) ገልፀዋል።

በትንበያው የቦረና፣ የጉጂ፣ የሲዳማና የደቡባዊ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ የተተነበየ ሲሆን፤ የደቡባዊ የሶማሌ ክልል አከባቢዎች ከመደበኛ በታች የዝናብ ሽፋን እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

የዝናብ ወቅቱ ፈጥኖ እንደሚገባና አስቀድሞ የሚወጣ መሆኑም ተገልጿል።

የደቡብ ምዕራብና የምዕራብ ኢትዮጵያ አከባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ሆኖ እንደሚቀጥልም ነው የተተነበየው።

በዚሁ የበጋ ወቅት በአብዛኛው የሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅ፣ የምስራቅና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ አከባቢዎች ከጥቅምት እስከ ህዳር ድረስ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊያጋጥም እንደሚችል ትንበያው ያሳያል።

በሙሉ ግርማይ