በሐረሪ ክልል በትምህርት ዘርፍ በተለይ በ12ኛ ክፍል ፈተና የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
"በቴክኖሎጂ የተደገፈ፤ ጥራት ያለው ትምህርት ለሀገር ብልፅግና" በሚል መሪ ቃል የ2018 የትምህርት ጉባዔ በሐረር መካሄድ ጀምሯል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፥ በተጠናቀቀው የ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት ነበር ብለዋል።
በተለይ በክልሉ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ለ12ኛ ክፍል ፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች 22 በመቶ የሚሆኑትን ማሳለፍ መቻሉ በክልሉ የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ ማሳያ መሆኑንም ገልፀዋል።
ትምህርት አገራችንን ወደ ቀድሞ ታላቅነትና ገናናነት ክብር የሚያሻግር ነው፣ መጪውን ዘመን ለመጪው ትውልድ፤ መጪውን ትውልድም ለመጪው ዘመን በማዘጋጀት ብልፅግናን ለማረጋገጥ ትምህርት የላቀ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በመሆኑም የትምህርት ጥራት፣ተደራሽነትና ተሳትፎን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ያሉ ሲሆን፤ አንድም ለትምህርት የደረሰ ልጅ ከትምህርት ገበታ እንዳይቀር ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስተር ዴኤታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ሥርዓቱ የነበሩ ስብራቶችን በመለየት እና ስትራቴጂዎችን በማውጣት በተሰራው ሥራ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ትምህርት ቤቶች ብቁና ለተማሪ ምቹ እንዲሆኑ እያስቻለ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዕለቱ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፤ በክልሉ ከ150 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተከናወኑ የትምህርት ቤት መሰረተ ልማቶችን ሥራ አስጀምረዋል።
በቴዎድሮስ ታደሰ