Search

የማንደራደርባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መቆም ይገባናል

ሓሙስ መስከረም 08, 2018 22

የማንደራደርባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መቆም ይገባናል ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ደቻሳ አበበ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልክ እንደ ዓድዋ ድል የራሱን ጠጠር በመወርወር የገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ እውን ሆኖ መመልከት ትልቅ ስኬት ነው ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ ዘንድ "ይጀምሩታል እንጂ አይጨርሱትም" የሚለውን አመለካከት የቀየረ፣ ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ እውን ሆኖ መመልከት የተቻለ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉ ገልፀዋል ፡፡
ኢትዮጵያውያን በብዙ መንገድ ኢ-ተገማች ህዝቦች ናቸው ተብሎ ይታመናል ያሉት ዶ/ር ደቻሳ፤ በዓድዋ ድል ወቅትም የውስጥ የእርስ በእርስ ችግሮች እና ቁርሾዎች የነበሩ ቢሆንም፤ ትልቅ የሀገር ጉዳይ ሲኖር ግን ትንንሽ ችግሮቻችንን ወደ ጎን በመተው ትልቁን የሀገር ጉዳይ ለመፈፀም እንደምንሰለፍ የታሪክ ገጠመኞቻችን በምስክርነት መነሳት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ሀገር በአንድ እለት አይሰራም ያሉት የታሪክ መምህር እና ተመራማሪው፤ አንድ ትውልድ ከሌላኛው ትውልድ ጋር በመቀባበል መሬት ላይ በሚታይ ሁነት ብቻ ሳይሆን በሥነ-ልቦናም ጭምር መገንባት አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የማንደራደርባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መቆም እንደሚገባ አንስተው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመገንባት በስራ ላይ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አሁንም በጋራ ከፍጻሜ ማድረስ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ሜጋ ፕሮጀክቶች ልክ እንደ ዓድዋ ድል እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁላችንም መሆናቸውን በማመን ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም ብለዋል፡፡
ለቀጣዩ ትውልድ ታሪካችንን የምናስተላፍበት እና ትርክቶቻችንን የምንገነባበት መንገድ በተለያየ መልኩ ሊሆን ይችላል ያሉት ዶ/ር ደቻሳ፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን በማጥበብ ለሀገራዊ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ