Search

የሕዳሴ ግድብ እውን መሆን በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ያለውን ኢፍትሐዊ ትርክት ቀይሮ፤ በአፍሪካ አዲስ መነቃቃትን ፈጥሯል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሓሙስ መስከረም 08, 2018 27

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፥  በወቅታዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ  ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ያለውን ፋይዳ እንዲሁም፤ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ የነበራትን ውጤታማ ተሳትፎ ዳሰዋል።

ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ-ካሪኮም ጉባዔ ላይ ስለነበራት የአስተናጋጅነት እና የተሳትፎ ሚና እንዲሁም በመጪው 80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ስለሚኖራት ተሳትፎ ቃል አቀባዩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ነብያት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፤ ኢትዮጵያ ቃላትን ወደ ተግባር የመቀየር ብቃቷን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አክለውም ፕሮጀክቱ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ያለውን ኢፍትሃዊ ትርክት ቀይሮ በአፍሪካ አዲስ መነቃቃትን ፈጥሯልም ነው ያሉት።

በቅርቡ በአዲስ አበባ በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ቃል አቀባዩ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ብቻ ሳትሆን አጀንዳ አቅራቢ መሆኗን አንስተው ይህም ሀገሪቱ በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም ያሳያል ብለዋል።

በሌላ በኩል በሁለተኛው የአፍሪካ-ካሪኮም የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ የአፍሪካና የካሪቢያን ግንኙነትን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ያሳየ እንደሆነ ገልፀው፤ ጉባዔውም በአፍሪካና የካሪቢያን  ታሪካዊ ግንኙነት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትብብር ላይ አፅንዖት የሰጠ እንደነበር ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በ80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንደምትሳተፍም አንስተው፤ ሀገሪቱ በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ የተከናወኑ ስኬቶችን፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት፣ በታዳሽ ኃይል ማስፋፋት ላይ የተከናወኑ ቁልፍ ተግባራትን እና ቀጣይ አጀንዳዎቿን ለማጉላት መድረኩን ትጠቀማለችም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ጉባዔው ጎን ለጎን አጋርነት እና ትብብርን ለማጠናከር የሁለትዮሽ ውይይትና ምክክር ለማድረግ መዘጋጀቷንም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

በሳምሶን በላይ